በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች የቀለብ እጥረት እንደገጠማቸው ገለጹ

58
ነቀምቴ ህዳር 9/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረ ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ባጋጠማቸው የቀለብ እጥረት መቸገራቸውን ገለጹ። በምስራቅ ወለጋ ዞን ሐሮ ሊሙ ወረዳ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አቶ አያና ጉዳታ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በመጠለያው በቂ ቀለብ ማግኘት ባለመቻላቸው ከስምንት ቤተሰቦቻቸው ጋር ለችግር ተጋልጠዋል። የተፈናቃዮች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት በመጠለያ ጣቢያው ከፍተኛ የቀለብ እጥረት መከሰቱን ጠቁመዋል። መምህር መለሰ ኦልጅራ የተባሉ ሌላው ተፈናቀይ በበኩላቸው ባለፉት ሦስት ወራት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ገልጸው በዚህ ምክንያት ከቤተሰባቸውና ከአቅመ ደካማ ወላጆቻቸው ጋር ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል። "በመጠለያ ጣቢያው የቀለብ እጥረት በማጋጠሙ በተለይ ሕጻናት በረሀብ እየተጎዱ ነው " ያሉት ደግሞ አቶ ጎበና አፋ የተባሉ ሌላ ተፈናቃይ ናቸው። " ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ ይስጠን " ብለዋል። የሐሮ ሊሙ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሮማ ቶለሳ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በወረዳው ለተጠለሉ ተፈናቃዮች በቂ ቀለብ ባለመቅረቡ ችግሩ ማጋጠሙን ተናግረዋል። የተፈናቃዮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 44 ሺህ 852 መድረሱን ገልጸው ተፈናቃዮች በየቀኑ ወደጣቢያው መምጣት ችግሩን ከወረዳው አቅም በላይ እንዳደረገውና ከፍተኛ የቀለብ እጥረት እንዲያጋጥም ምክንያት መሆኑን አስረደትዋል። መንግስት ለተፈናቃዮች ቶሎ ካልደረሰላቸው ከፍተኛ የሆነ የቀለብ ችግር እንደሚጋረጥባቸው ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል፡፡ የምስራቅ ወለጋ ዞን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳርጌ ጉደታ በበኩላቸው "ቀደም ሲል በወረዳው የደረሰው ቀለብ ከተፈናቃይ ብዛት አንጻር በቂ እንዳልነበር ተረጋግጧል" ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ለሁለተኛ ዙር ቀለብ እንዲደርስ ለበላይ አካል ጥያቄ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። የተከሰተውን የቀለብ እጥረት ለማቃለል እንዲቻል ለክልሉ መንግስት በማሳወቅ መፍትሄ በማፈላለግ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ በቀለ ናቸው።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም