ኢትዮጵያ በቀጠናው ለውጥ ላይ እያደረገች ያለው አስተዋጽኦ የሚደነቅ መሆኑን ጅቡቲ አስታወቀች

54
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦመር ጊሌ በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ተወያይተዋል።  አዲስ አበባ ህዳር 9/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአገር ውስጥ እና በቀጠናው እያመጡት ያለው ለውጥ የሚደነቅ መሆኑን የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦመር ጊሌ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጅቡቲና ኤርትራ ችግሮቻቸውን በመነጋገር እንዲፈቱ እያከናወኑት ላለው ተግባርም ፕሬዝዳንቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማህሙድ አሊ የሱፍ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በርካታ የሚጋሯቸው ጉዳዮች እንደመኖራቸው መጠን አገራቱ በንግድና ኢንቨስትመንት በሰፊው ተሳስረዋል። ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦመር ጊሌ ይህ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚፈልጉ በውይይቱ ማንሳታቸውን የተናገሩት ሚንስትሩ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እያመጧቸው ላሉት ለውጦች ፕሬዝዳንቱ አድናቆት እንደቸሯቸውም አውስተዋል። "የኤርትራና ጅቡት ግንኙነት እንዲሻሻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየሰሩት ላለው ስራ እናመሰግናለን" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ መስራቷንም ጠቁመዋል። ጅቡቲ ቀጠናው ሰላም እንዲሆን እና እንዲተሳሰር አበክራ የምትሰራ መሆኑንም አንስተዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው፤ የሁለቱ አገራት መሪዎች በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት እንዳደረጉ ነው የተናገሩት። ኤርትራ ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ መነሳቱ  ለቀጠናው መልካም መሆኑን ሁለቱ አገራት ማንሳታቸውን ጠቁመው፤ ኤርትራና ጅቡቲ በመካከላቸው ያሉ ችግሮችን  በሰላም እንዲፈቱ ኢትዮጵያ የበኩሏን ሁሉ ድርሻ እንደምትወጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማረጋገጣቸውንም ገልጸዋል። ኤርትራና ጅቡቲ በማካከላቸው ያሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ እንደምትወጣ ጠቅላይ ሚነስትሩ ማረጋገጣቸውንም ጨምረው ገልጸዋል። በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ከግብፁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቦሊ ጋር በሁለቱ አገራት የጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በውይይታቸውም በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነትን በተለይም የጋራ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ መክረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም