የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቀጣይነትን ለማጠናከር ሁሉም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ተባለ

74
አዲስ አበባ ህዳር 9/2011 "ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  ስፖርታዊ ክዋኔን ሁሉም ሊጠበቅውና ሊንከባከበው ይገባል" ሲል ኡጋንዳዊ የማራቶን ሯጭ አትሌት ስቴቨን ኪፕሮቲች ገለጸ። አትሌት ስቴፈን ኪፕሮቲች ለ18ኛ ጊዜ በተካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የክብር እንግዳ ሆኖ ተገኝቷል። አትሌቱ እኤአ በ2012 የለንደን ኦሎምፒክና በ2013 የሞስኮ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድሮች በማራቶን ለሀገሩ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣ ስፖርተኛ ነው። ከውድድሩ በኋላ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ በማድረግና ህዝቡም በቀጣይነቱ ላይ የራሱን ሚና በመወጣት ስፖርታዊ ኩነቱን ሊያሳድገው እንደሚገባም ጠቅሷል። በሀገሩ ኡጋንዳ በአንድ የሞባይል አምራች ኩባንያ የሚደገፍ ይህን መሰል ውድድር እንዳለ የተናገረው አትሌቱ "በተሳታፊ  ብዛቱም ሆነ በድምቀቱ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያጋር የሚነጻጸር አይደለም" ብሏል። ''ዛሬ በአዲስ አበባ ያየሁት ውድድር በጣም አስደናቂና አስገራሚ ድባብ ያለው ነው'' ሲልም ገልጿል። ውድድሩ ደማቅ ሆኖ እንዲቀጥል ከተፈለገ የአዘጋጆቹ ስራ ብቻ ሆኖ ሊተው እንደማይገባም አሳስቧል። ከ18 ዓመት በፊት 10 ሺህ ሰዎችን በማሳተፍ የተጀመረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተሳታፊዎችን ቁጥር በየጊዜው እያሳደገ በመምጣት አሁን ላይ 44 ሺህ ህዝብ ማሳተፍ ችሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም