በዲላ ከተማ ዛሬ ረፋድ ላይ የተከሰተው ግጭት በቁጥጥር ስር ውሏል- የዞኑ ጸጥታና አስተዳደር መምሪያ

85
ዲላ ግንቦት 15/2010 በዲላ ከተማ ዛሬ ረፋድ ላይ በተማሪዎች መካከል በተነሳ የቡድን ጸብ ምክንያት በከተማው ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት መቆጣጠሩን የጌዲኦ ዞን ጸጥታና አስተዳደር መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ሃላፊ አቶ እንግዳወርቅ ዳካ ለኢዜአ እንደገለጹት በዲላ መሰናዶና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለት ተማሪዎች መካከል በተነሳ ጸብ አንደኛው በስለት መወጋቱን ተከትሎ በከተማው የጸጥታ ችግር ተፈጥሮ ነበር። ከሁሉም የጸጥታ አካላት የተውጣጣ ሃይል ሁኔታውን ለመቆጣጥር ርብርብ ያደረገ ሲሆን በሃይማኖት መሪዎች በኩል በየአካባቢው ያሉ ወጣቶችን በማረጋጋት ወደየቤታቸው እንዲገቡ መደረጉንም ተናግረዋል። በጸጥታው ችግር ምክንያት በሌሎች ሰዎች ህይወት ላይ ጉዳት አለመከሰቱን የገለጹት ኃላፊው "በሶስት ተሸከርካሪዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሷል" ብለዋል። ተማሪው ላይ ጉዳት ያደረሱትን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊስ ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በነገው እለትም በከተማዋ ከሚኖሩ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እንደሚካሄድ ተናግረዋል። በስለት የተወጋው ተማሪ የህክምና እርዳታ ሲደረግለት ቢቆይም ማምሻውን ህይወቱ ማለፉን ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም