የካንስር ምርምርና ሕክምና ማዕከሉ በመጪው ጥር ወር አገልግሎት መስጠት ይጀምራል

104
ጎንደር ህዳር 9/2011 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ150 ሚሊዮን ብር ወጪ እያስገነባው ያለው የካንስር ምርምርና ሕክምና ማዕከል በመጪው ጥር ወር ለካንሰር ታማሚዎች የጨረር ሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሲሳይ ይፍሩ ለኢዜአ እንደተናገሩት የጨረር ሕክምናውን ለማስጀመር እንዲቻል በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዙ 2 የጨረር ሕክምና መስጫ መሳሪያዎች በታህሳስ ወር ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው ባለስድስት ፎቅ የካንስር ምርምርና ሕክምና ማዕከል በአሁኑ ወቅት የጨረር ህክምናውን ለማስጀመር የሚያስችሉት ሦስት ፎቆች ሙሉ በሙሉ ግንባታቸው መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶክተር ሲሳይ ገለጻ ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ተከላቸው የሚከናወነው የጨረር ሕክምና መስጫ መሳሪያዎች በጥር ወር የተሟላ የጨረር ሕክምና አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ፡፡ የጨረር ሕክምናው የሚሰጠው በጡት፣ በአንጀትና በማህጸን ጫፍ ካንስር ለረጅም ወራት በበሽታው ለተጠቁ ህሙማን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ "የሕከምና መሳሪያዎቹ በቀን ከ16 እስከ 20 ለሚሆኑ የካንስር ሕሙማን የጨረር ሕክምና ለመስጠት ያስችላሉም" ተብሏል፡፡ በሆስፒታሉ የጨረር ሕክምና አገልግሎት ለመጀመር መታቀዱ ከዚህ ቀደም የጨረር ሕክምና ለማግኘት ወደአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚላኩ የካንሰር ሕሙማን ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት ያስቀራል፡፡ የካንሰር ታማሚዎች ወደ አዲስ አበባ ሲላኩ የጨረር ሕክምና ለማግኘት ከ9 እስከ 12 ወራት ወረፋ ስለሚጠብቁ ካንሰሩ ተስፋፍቶ በጤናቸው ላይ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱንም ዶክተር ሲሳይ በማሳያነት ጠቅሰዋል። ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት ባቋቋመው ጊዚያዊ የካንስር ሕክምና መስጫ ክፍል ከ700 በላይ ለሚደርሱ ተመላላሽ የካንስር ታማሚዎች ምርመራን ጨምሮ የመድኃኒትና የቀላል የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ባለስድስት ፎቅ የካንስር ምርምርና ሕክምና መስጫ ማዕከሉ ህንጻ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም 100 የሕክምና አልጋዎች እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡ "ማዕከሉ ከካንስር ሕክምና ጎን ለጎን በበሽታው ስርጭት ላይ ጥልቀት ያላቸው ምርምሮችን በማካሄድ በሽታውን ለመከላከል በሚቻልበት መንገድ ላይ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል ዶክተር ሲሳይ ፡፡ በሆስፒታሉ ጊዚያዊ የካንስር ሕክምና ክፍል የካንሰር ሕክምና ከሚከታተሉ ሕሙማን መካከል አቶ ሲራጅ ሰይድ በሰጡት አስተያየት በአንጀት ካንስር ታመው ቀዶ ሕከምና ተደርጎላቸው በማገገም ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ "ሆስፒታሉ የጨረር ሕክምና ለመስጠት ማቀዱ ትልቅ የምስራች ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ሞላ ሲሳይ የተባሉ የካንሰር ታማሚ ናቸው፡፡ ለጨረር ሕክምና አዲስ አበባ የሚላኩ በርካታ የካንሰር ታማሚዎች በገንዘብ እጥረት ማነስ ሳቢያ መሄድ ሳይችሉ ቀርተው በቤታቸው ሞታቸውን እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በአመጋገብና በአኗኗር ዘዬ መቀየር ምክንያት እየተስፋፋ የመጣውን የካንሰር በሽታ ስርጭት ለመግታት መንግስት በተመረጡ አካባቢዎች የካንሰር ሕክምና መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም ላይ ይገኛል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም