የድሬዳዋ ወጣቶች ከተማቸው በእግር ኳስ የነበራትን ገናና ስም ለመመለስ ትኩረት እንዲሰጥ ጠየቁ

67
 ድሬዳዋ ህዳር 9/2011 ድሬዳዋ በእግር ኳስ የነበራትን ገናና ስም ለመመለስ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ  ወጣቶች ጠየቁ። ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በስፖርቱ ውስጥ ያለፉት ስፖርቱን እንዲመሩትና እንዲደግፉት ይደረጋል ብለዋል፡፡ ወጣቶቹ ሰሞኑን ከድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባና አመራሮች ጋር በስፖርት በተለይም  በእግር ኳስ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ተወያይተዋል፡፡ ወጣቶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ከተማዋ ከሁለት አሥርት አመታት  በፊት የአገሪቱ ምርጥ  እግር ኳስ ተጫዋቾች መፍለቂያና አውራ ነበረች፡፡ አሁን ግን ይህ ታላቅ ስሟ ተሸርሸሮ ጭራ ሆናለች ብለዋል፡፡ ወጣት ሱሌይማን ዓሊ በሰጠው አስተያየት አስተዳደሩ ለስፖርት የሚመድበው በጀት ከፍተኛ ቢሆንም፤ ከተማዋን ወክሎ  በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ብቸኛ ክለብ በየዓመቱ ላለመውረድ የሚተጋ ክለብ ሆኗል።ሂደቱን መቀየርና ዝናዋን ለመመለስ መሥራት ያስፈልጋል ብሏል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ናትናኤል ሥዩም በትምህርት ቤቶችና በቀበሌዎች የተቋቋሙ የፕሮጀክት ሰልጣኞች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መከታተልና መደገፍ እንደሚያስፈልግና ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚያሻ ይገልጻል፡፡ ስፖርት የማያውቁ ሰዎች ከ10 ዓመታት በላይ በመምራታቸው ዕድገቱ ቀጭጯል በማለት ቅሬታዋን የገለጸችው ደግሞ ወጣት ፈቲሃ አህመድ የተባለች ነዋሪ ናት፡፡ ድሬዳዋ ከነማን ለመደገፍ እያባከንሁት ያለሁት የሥራ ጊዜ፣ የማወጣው ወጪና ጉልበት እየቆጨኝ መጥቷል የሚለው ወጣት ሰለሞን ብርሃኑ አስተዳደሩ ክለቡን በማፍረስ በጀቱን በታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ሊያውለው ይገባልም ብሏል። ወጣት አዚዛ አብዲ በስፖርቱ ዘርፍ የተፈጠረውን ክፍተት ለማረም የስፖርት ቤተሰቦች ከስፖርት ኮሚሽን ጋር ተቀናጅተው ለውጥ ለማምጣት እንዲሰሩ ትመክራለች። ወጣት አዚዛ አብዲ በስፖርቱ ዘርፍ የተፈጠረውን ክፍተት ለማረም የስፖርት ቤተሰቦብ ከስፖርት ኮሚሽን ጋር መፍትሄውን በጋራ  ለማምጣት እንደሚገባና በተለይ ለረዥም ዓመታት በመጫወትም ሆነ ክለብን በመምራት ያሳለፉ ሰዎች ስፖርቱን በቅርበት መደገፍ ይገባቸዋል ብላለች፡፡ ወጣት ናሆም ኃይሉ እግር ኳሱን እያቀጨጨ የሚገኘው መንደርተኝነትና የአመራሩ ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ገልጾ፣ ክፍተቶቹን በማረም ብቃትና ችሎታ ያላቸው ስፖርተኞች ማፍራት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን አስተዳደሩ በዘርፉ ላይ ሥር -ነቀል ለውጥ ለማምጣት በተለይ በታዳጊ ወጣቶች ላይ በስፋት በመሥራት የከተማዋን ገናናነት ለመመለስ  መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።ለዚህም ስፖርቱን በብቃትና በችሎታ የሚመራ ጠንካራ አሠራርና አደረጃጀት ይዘረጋል፡፡ ''ልክ የቦክስና የሣይክል(የቢስክሌት ፌደሬሽኖችን በስፖርቱ ውስጥ ባለፉ አካላት እንዲመሩና ለውጥ እንዲመጣ የተሰራው ሥራ በእግር ኳሱም ላይ በመድገም ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚመጣ ይሰራል'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የአስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ከድር ጁሃር በበኩላቸው ስፖርቱን በሠፈርተኝነት፣ በዝምድና በገንዘብ ከመጠቃቀም በማላቀቅ የቀድሞ ብርቅና ድንቅ ተጫዋቾችንን ዝና የሚመልሱ ብቃትና ችሎታ ያላቸው  አዳጊዎችን ለማፍራት ይሰራል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት አሰልጣኞች ላይ የሚስተዋለውን የሙያና የክህሎት ክፍተት የሚሞላ ሥልጠና እንደሚሰጥበት አመልክተዋል፡፡ አካዳሚው የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በ221 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አካዳሚው ከ15 ና ከ17 ዓመት በታች የሆኑ 200 ስፖርተኞች ማደሪያ፣የስፖርት መከወኛና መጫወቻዎች ይኖሩታል። በሁለት ዓመታት ግንባታው ለሚከናወነው አካዳሚ ጨረታ በመውጣት ሂደት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም