በድሬዳዋ የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዝ ፕሮጀክት ሊተገበር ነው

62
ድሬዳዋ ህዳር 9/2011 በድሬዳዋ የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የሚያግዝ ፕሮጀክት በ30 ሚሊዮን ብር እንደሚተገበር የአስተዳደሩ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አማኑኤል ፍስሃ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት የዝግጅት ምዕራፍ ትናንት በተገመገመበት ወቅት እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ለሦስት ዓመታት በሁለት ገጠር ቀበሌዎች በሙከራ ደረጃ ይተገበራል። ፕሮጀክቱ በዋሂል እና በለገኦዳን ቀበሌዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚያግዝ ገልጸው፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ፣ በችግኝ ተከላና ክብክባቤ፣ በእንስሳትና አዝርዕት ልማት ላይ በማተኮር የሚተገበር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ አማኑኤል አንዳሉት በዝግጅት ምዕራፉ በአስተዳደሩ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንና የግብርና ቢሮ ቅንጅት በመፍጠር  ያከናወኗቸው ሥራዎች በጥሩ ደረጃ ይገኛሉ፡፡ በአስተዳደሩ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዳዊት ዮሴፍ በበኩላቸው እንዳሉት በሚቀጥሉት 3 ዓመታት በ30 ሚሊዮን ብር የሚተገበረው ፕሮጀክት 11 ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል። ይህም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና እንደሚያረጋግጥ ገልጸው፣ ፕሮጀክቱ ድሬዳዋን ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ14 ወረዳዎች እንደሚተገበር ጠቁመዋል፡፡ "በቀጣይ የፕሮጀክቱ ውጤታማነት ታይቶ የበጀትና የተጠቃሚው ቁጥር ይጨምራል" ያሉት አቶ ዳዊት በፕሮጀክቱ የገጠሩን ምርትና ምርታማነት  ከማሳደግ ጎን ለጎን አርሶ አደሩ የላቡ ውጤት ተጠቃሚ እንዲሆን ከገበያ ጋር የማስተሳሰር ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የግብርና ባለሙያ አቶ ያለው አርአያ በበኩላቸው "ፕሮጀክቱ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ሕይወት ከመለወጥ ባለፈ  የአስተዳደሩ ግብርና ቢሮ የሚያከናውናቸውን ሥራዎችን ያግዛል" ብለዋል፡፡ አቶ ያለው እንዳሉት በፕሮጀክቱ ትግበራ በጥናት ላይ የተመሰረተ የውሃ ሃብት መጠንን ከመቃኘት ባለፈ የውሃ ማጠራቀሚያ ኩሬዎች ይሠራሉ፤ ሰፋፊ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ተግባራትም ይከናወናሉ፡፡ የዝግጅት ምዕራፉ የተገመገመው ይህ ፕሮጀክት ከተያዘው ህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ይሸጋገራል ተብሏል፡፡                                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም