በማቻከል ወረዳ የግብርና ምርታማነትን ከእጥፍ በላይ ማሳደግ ተችሏል

1332
ደብረማርቆስ ግንቦት 15/2010 በማቻከል ወረዳ ባለፉት ዓመታት የግብርና ምርታማነትን ከእጥፍ በላይ ማሳደግ ተችሏል ተባለ፡፡ በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻካል ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር መንግስት አዳነ የግብርና ሥራቸውን ከቤተሰብ በልምድ ባገኙት ባህላዊ አሰራር ለዓመታት ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ይህም ለቤተሰብ ቀለብ የሚሆን ምርት ብቻ እንዲያገኙ ከማድረግ ውጭ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሳያደርጋቸው ቆይታል ፤ "ያኔ በዘመናዊ የግብርና ዘዴ ምርታማነት ለማሳደግ ግንዛቤውም ሆነ እውቀቱ አልነበረኝም ይላሉ። ከግንቦት 20 ማግስት በኋላ ግብርናውን ለማዘመንና የአርሶአደሩን ምርታማነት ለማሳደግ መንግስት ተገቢ ትኩረት በመስጠቱ ከግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ምክርና ስልጠና በማግኘት የግብርና አሰራራቸውን እንዳሻሻሉ ተናግረዋል። በእዚህም ባለፉት ዓመታት የምርት ማሳዳጊያና የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም በሄክታር ያገኙት የነበረውን ምርት ከእጥፍ በላይ ማሳደግ መቻላቸውን ነው የገለጹት። በተለይ በመስመር መዝራት፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዲሁም ፀረ አረምና ተባይ መከላከያ መድኃኒት መጠቀም በመቻሌ ቀደም ሲል ከአንድ ሄክታር አገኝ የነበረውን ምርት ከእጥፍ በላይ አሳድጎልኛል" ይላሉ። በእዚህም ቀደም ሲል በአንድ ሄክታር 20 ኩንታል ስንዴ ምርት ያገኙ የነበረው በአሁኑ ወቅት ከ70 ኩንታል በላይ በመሰብሰብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው በማሳያነት የጠቀሱት። "ቀደም ባሉት ጊዜያት ኑሮን ለመደጎም ልጆቼን በሰው ቤት እስከማስቀጠር ደርሼ ነበር" ያሉት አርሶ አደር መንግስት፣ ባለፉት ዓመታት ምርታማ በመሆናቸው የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውንና ሁለት ለጆቻቸውን አስተምረው በመጀመሪያ ዲግሪ ለማስመረቅ መቻላቸውን ተናግረዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ዘመናዊ የግብርና አሰራር ብዙም ባለመዘውተሩና በቂ እውቀት ስላልነበር ብዙ ማሳ ቢኖራቸውም ከእጅ ወደ አፍ ያልዘለለ ምርት ያመርቱ እንደነበር የገለጹት ደግሞ የተሳዳር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ስመኘው አለማየሁ ናቸው። ከግንቦት ሃያ ማግስት ለግብርና እድገት ትኩረት በመሰጠቱ  በአካባቢያቸው የግብርና ሰርቶ ማሳያዎች ተቋቁመው ልምድ እና ተሞክሮ ከመቅሰማቸው ባለፈ በመስኖ ጭምር እንዲያለሙ መደረጉ ምርታማ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። እንደ አርሶአደር ስመኘው ገለጻ፣ ቀደም ሲል ማዳበሪያ ሳይጠቀሙ በአንድ ሄክታር ከስምንት ኩንታል ማይበልጥ ጤፍ ያመርቱ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ማዳበሪያን በመጠቀምና መሳን ደጋግሞ በማረስ ምርታቸውን ከሦስት እጥፍ በላይ ማሳደግ ችለዋል። ከሰብል ምርት ጎንለጎን በአትክልትና ፍራፍሬን ልማት በመሳተፍ በዓመት ከ12 ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ እንደሚያገኙና በእዚህም በላፉት ዓማታት ከ120 ሺህ ብር በላይ መቆጠባቸውን ነው የገለጹት። የማቻከል ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ላሽተው መኩሪያው በበኩላቸው ከልማዳዊ አሰራር በመላቀቅ ኩትቻ አፈር በማጣፈፍ፣ ሰብልን በመስመር በመዝራት፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመጠቀም የግብርና ስራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። "በእዚህም በ3 ሄክታር መሬታቸው ላይ በቆሎና ስንዴ በማምረት በመኪና አስጭኜ እስከመሸጥና ተሸላሚ አርሶ አደር እስከመሆን ደርሼአለሁ" ብለዋል። ጊዜው የአርሶ አደር መሆኑን የተናገሩት አርሶ አደሩ ላሽተው "ጠንክሮ የሰራ የሚሸለምበት፤ በጥራትና በብዛት ላመረተም በቀጥታ ለፋብሪካ የሚያስረክብበት ዕድል ተፈጥሯል። ይህ ደግሞ የግንቦት 20 ውጤት ነው" ብለዋል። አርሶ አደሩ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን አሰራሮችን እንዲጠቀም በማድረግ በሄክታር ያገኝ የነበረውን ምርት መሳደግ እንደተቻለ የገለጹት ደግሞ የወረዳው ግብርና ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ካሳ ናቸው። በተሰራው ሥራም ቀደም ሲል በወረዳው ከ600 ሺህ ኩንታል የማይበልጥ የነበረው ዓመታዊ የምርት መጠን በአሁኑ ወቅት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ የተቻለበት ጊዜ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም