አትሌት ሀጎስ ገብረህይወትና ፎቴን ተስፋዬ የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሸናፊ ሆኑ

76
አዲስ አበባ ህዳር 9/2011 ዛሬ በተካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በወንዶች አትሌት ሀጎስ ገብረህይወትና በሴቶች አትሌት ፎቴን ተስፋዬ አሸነፉ። መነሻና መድረሻውን ስድስት ኪሎ ሰማእታት አደባባይ ያደረገውና 44 ሺህ ሰዎችን ያሳተፈው 18ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድደር በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል። በውድድሩ ከሁለት ዓመት በፊት በሪዮ ዲጄነሪዮ ኦሎምፒክ በ5 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊውና እኤእ በ2013 እና 2015 የሞስኮና ቤጂንግ የአለም ሻምፒዮና፤ በ5 ሺህ ሜትር የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት አትሌት ሀጎስ ገብረህይወት አሸናፊ ሆኗል። አትሌት ሀጎስ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 28 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ ከ3 ማይክሮ ሴኮንድ ወስዶበታል። ይህን ውድድር ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀው ቦንሳ ዲዳ ሲሆን ውድድሩን ለማጠናቀቅ 29 ደቂቃ ከ3 ሴኮንድ ከስምንት ማይክሮ ሴኮንድ ፈጅቶበታል። ቦንሳን ተከትሎ በመግባት ሶሰተኛ የሆነው አትሌት ጥላሁን አየን 29 ደቂቃ ከ13 ሴኮንድ ከ7 ማይክሮ ሴኮንድ በሆነ ሰዓት ነው። በሴቶች መካካል የተደረገውን ውድድር ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት ለ16ኛ ጊዜ በተደረገው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሸናፊ የነበረችው አትሌት ፎቴን ተስፋዬ በአንደኝነት አጠናቃለች። ውድድሩንም ለማጠናቀቅ 33 ደቂቃ ከ43 ሴኮንድ ከ5 ማይክሮ ሴኮንድ ወስዶታል። በውድድሩ በሁለተኛ የሆነችው አትሌት ፀሀይ ገመቹ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 33 ደቂቃ ከ48 ሴኮንድ ከ8 ማይክሮ ሴኮንድ ወስዶባታል። አትሌት ፀጋ ገብረሰላማ ደግሞ 33 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ከስምንት ማይክሮ ሴኮንድ በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በዚህ ውድድር ለአሸናፊ አትሌቶች የ100 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ላጠናቀቁ ደግሞ የ30 እና 15 ሺህ ብር ሽልማት እንደየደረጃቸው ተሸላሚ ሆነዋል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከጤና ሯጮች በተጨማሪ አራት ኤርትራዊያንን ጨምሮ ከተለያዩ የውጭ አገራት የመጡ አትሌቶችንም አሳትፏል። በአትሌቶች መካከል በተደረገው ውድድር  ከዩጋንዳ ኬኒያና ቦትስዋና የመጡ አትሌቶች ተካፍለዋል። በግማሽ ማራቶን ታዋቂ የሆነው ኤርትራዊው  አትሌት ዘረሰናይ ታደሰና የማራቶን ሯጭ ዩጋንዳዊው ስቴቨን ኪፕሮቲች በክብር እንግድነት ተግኝተዋል። የዚህ ውድድር መስራች ሻለቃ አትሌት ኋይሌ ገብረ ስላሴ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ ውድድሩ እንደባለፈው ዓመት ሁሉ በጥሩ ሁኔታ ተካሂዷል ብሏል። ከቦታ ለውጥ ጋር ተያይዞ ውድድሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች የተወሰነ መጉላላት የሚፈጥር ቢሆንም ህዝቡ ላሳየው ትዕግስትና ትብብር  ምስጋናውን አቅርቧል።                                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም