የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀማችን ምርታማነታችንን አሳድጎታል....የምዕራብ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች

65
አምቦ ህዳር 9/2011 የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ምርታማነታቸው ማደጉን አንዳንድ የምዕራብ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ። በዞኑ በዚህ ዓመት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ እየተሰራ ነው። በምዕራብ ሸዋ ዞን የደንዲ ወረዳ አርሶ አደር በቀለ ነጋሳ እንዳሉት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ሰፊ ጉልበት ቢጠይቅም ጠቀሜታው የጎላ ነው። በአካባቢ ከሚገኝ ፍግ፣ አመድ፣ ቅጠላቅጠልና ከሌሎችም ግብዓት የሚያዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ የመሬት እርጥበትንና ለምነትን ጠብቆ በማቆየት የተሻለ ምርት ለማግኘት እያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ በፊት የፋብሪካ ማዳበሪያ በመጠቀም በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ከሚያለሙት ቀይ ሽንኩርት 30 ኩንታል ምርት ብቻ ሲያገኙ እንደነበር አስታውሰው በተፈጥሮ ማዳበሪያ ምርታማነታቸውን ወደ 40 ኩንታል ማሳደግ እንደቻሉ ገልጸዋል። " የተፈጥሮ ማዳበሪያ አንድ ጊዜ በመጠቀም ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ተጨማሪ ማዳበሪያ ሳያስፈልግ በቂ ምርት እያገኘሁ ነው " ያሉት ደግሞ የሊበን ጃዊ ወረዳ አርሶ አደር ቢሊሱማ ረጋሳ ናቸው ፡፡ በየዓመቱ ከሰብል ተረፈ ምርትና ፍግ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ለመስኖና ለመኽር ልማት እንደሚያውሉ የሚናገሩት አርሶ አደሩ ይህም የማዳበሪያ ወጪያቸውን ለመቀነስ እንዳስቻላቸው ነው የገለጹት። አርሶ አደር ቢሊሱማ እንዳሉት ባለፈው ዓመት ብቻ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ካለሙት አንድ ሄክታር የበቆሎ ማሳ ከ80 ኩንታል በላይ ምርት አግኝተዋል። ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮችም እንዳሉት የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ምርታማነታቸውን ከማሳደግ ባለፈ ለሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ሲያወጡ የነበረውን ወጪ በግማሽ መቀነስ ችላዋል። የምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የአፈር ልማት ማሻሻያ ቡድን ባለሙያ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ቀቀባ በበኩላቸው "በዞኑ የግብርና ምርትን በዘላቂነት ለማሳደግ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቃሚ እንዲሆን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል" ብለዋል። በተያዘው ዓምትም ከ1 ነጠብ 1 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያን ለማዘጋጀት በዞኑ 22 የገጠር ወረዳዎች እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ ከ224 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው። እስካሁንም ከ118 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ነው የጠቆሙት። ወይዘሮ ዓለምጸሐይ እንዳሉት በአርሶ አደሩ ጉልበት እየተዘጋጀ ያለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከዓምናው ጋር ሲነጻጸር በ500 ሺህ ሜትር  ኪዩብ ብልጫ አለው፡፡ በአርሶ አደሮቹ የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያም 14 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው። እንደ ባለሙያዋ ገለፃ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ምርታማነትን በማሳደጉ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ የተሳታፊ አርሶ አደሮች ቁጥር በየዓመቱ እያደገ መጥቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም