የትራፊክ አደጋ በሰው ህይወትና አካል ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ኀብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

114
አዲስ አበባ  ህዳር  8/32011  የትራፊክ አደጋ በሰው ህይወትና አካል ላይ የሚያደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ኀብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ጥሪ አቀረበ። ድርጅቱ አደጋን ተከላክሎ በማሽከርከር ውጤት ላስመዘገቡ 150 የአውቶቡስ አሽከርካሪዎች የማበረታቻና የእውቅና ስነ ስርዓት አካሂዷል። በአሽከርካሪነት ከአንድ እስከ አራት ዓመት ድረስ ምንም ዓይነት አደጋ ያላደረሱና ያልደረሰባቸው አሽከርካሪዎችን ከምስክር ወረቀት ጀምሮ እስከ የወርቅ ሜዳሊያ ድረስ ተበርክቶላቸዋል። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ትልቁ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካይ ለ5 ሺህ ሰዎች ህልፈተ ህይወት ምክንያት የሆነው የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ አይደለም። ''ጥይት አልባ ጦርነት የሆነውን የትራፊክ አደጋ የመከላከል ስራ የሚጀመረው ከቤት ነው'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ ወላጆች ስለመንገድ አጠቃቀም ለልጆቻቸው ግንዛቤ መስጠትን በትኩረት ሊተገብሩት እንደሚገባ ገልጸዋል። የትራፊክ አደጋ የመከላከል ሥራ ለአንድ ተቋም የሚተው ባለመሆኑ ኀብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል። አገራዊ ልማቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚጠፋውን አምራች ዜጋ ቁጥር ለመቀነስ ድርጅቱ በአውቶቡስ አሽከርካሪዎች ቅጥር ላይ በጥንቃቄ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዛሬው ዕለት አደጋ ሳያደርሱ ላገለገሉ የአውቶቡስ አሽከርካሪዎች የተሰጠው እውቅና ድርጅቱ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል እየሰራ ላለው ተግባር ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም