ድርጅቱ ለ50 ህፃናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

60
አዲስ አበባ ህዳር 8/3/2011 የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ስር ለሚገኙ 50 ህፃናት የቦርሳና የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ ድጋፍ አደረገ። ድርጅቱ 40 ሺህ ብር ግምት ያለውን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለህፃናቱ ያደረገው አደጋ ሳያደርሱና ሳይደርስባቸው ላሽከረከሩ የባስ ካፒቴኖቹ እውቅና በሰጠበት ስነ-ስርዓት ላይ ነው። የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታደለ አየለ ማህበሩ ለ614 ህፃናት የትምህርት ቁሳቁስና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ከእነዚህ መካከል 150 ህፃናት ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ በሚገኘው የማህበሩ ግቢ እየኖሩ ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። ማህበሩ 450 እናቶች ራሳቸውን እንዲችሉ ስልጠናና ድጋፍ እየሰጣቸው እንደሆነም አክለዋል። ከፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሰራተኞች ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ሌሎች ድርጅቶችና ግለሰቦችም ማህበሩን በመጎብኘት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ትልቁ በበኩላቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን የመወጣት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።     ---END---  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም