የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ አሽከርካሪዎች ክህሎትና መልካም ስነ-ምግባር ሊኖራቸው ይገባል

73
አዲስ አበባ ህዳር 8/2011 አቶ ታምራት ወልደ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ጎዳናዎች ለ32 ዓመታት ሲያሽከረክሩ በሌሎች አሽከርካሪዎች ከደረሰባቸው መገጨት በቀር አንድም ጊዜ የትራፊክ አደጋ እንዳላደረሱ ይናገራሉ። አሁን የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የአውቶቡስ ካፒቴን ሲሆኑ በድርጅቱ ባሳለፏቸው አራት ዓመታትም ምንም አይነት አደጋ ባለማድረሳቸውና በእርሳቸውም ስላልደረሰባቸው ድርጅቱ የወርቅ ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ሸልሟቸዋል። አቶ ታምራት ለ32 ዓመታት ምንም አይነት የትራፊክ አደጋ ሳያደርሱ የመዝለቃቸው ምስጢር በመልካም ስነ-ምግባር የትራፊክ ህግና ደንብ ማክበራቸው ነው። በአገሪቱ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቀነስ አሽከርካሪዎች ክህሎትና መልካም ስነ-ምግባር ያላቸው መሆን እንዳለባቸው ነው የገለጹት። የመንጃ ፍቃድ አሰጣጡ ላይ ያሉ ችግሮችን ማስወገድ እንደሚገባና በተቋማት ለሚገኙ አሽከርካሪዎች የሚሰጡ የስራ ላይ ስልጠናዎች ለሌሎችም አሽከርካሪዎች የሚሰጥበት ሁኔታ ቢመቻች የትራፊክ አደጋን የመቀነስ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም ተናግረዋል። ሌላው የአውቶቡስ ካፒቴን ኤልያስ አብዱ በበኩሉ ማሽከርከር ከጀመረ ዘጠኝ ዓመት እንደሞላውና ምንም አይነት አደጋም እንዳላደረሰ  ተናግሯል። በካፒቴን ኤልያስም በድርጅቱ ለሶስት ዓመት ምንም አደጋ ያላደረሰና ያልደረሰበት በሚል የብር ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል። ኤሊያስ አሽከርካሪዎች ራሳቸውን ከሱስ ማፅዳትና የሙያ ስነ-ምግባር ጠብቀው በማሽከርከር ለትራፊክ አደጋ መቀነስ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው መክሯል። በድርጅቱ ከተቀጠረ ሁለት ዓመት የሞላውና ለአንድ ዓመት ያለ ምንም አደጋ በማሽከርከሩ የምስክር ወረቀት የተበረከተለት የባስ ካፒቴን ደመላሽ መሸሻ በበኩሉ ፍጥነትን ጠብቆ በንቃትና በትጋት በማሽከርከር 'የትራፊክ አደጋን መቀነስ ይገባል' ብሏል። ተሸላሚዎቹ የባስ ካፒቴኖች እውቅናና ሽልማቱ በቀጣይም በኃላፊነት እንዲያሽከረክሩ የሚያነቃቃቸው መሆኑን ገልጸዋል። የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ምንም የትራፊክ አደጋ ሳያደርሱና ሳይደርስባቸው ከአንድ ዓመት እስከ አራት አመት ላሽከረከሩ 150 የባስ ካፒቴኖች እውቅና ሰጥቷል። ድርጅቱ በ2007 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በቀን በአማካይ 11 ሺህ ተሳፋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርግ የነበረ ሲሆን አሁን በቀን በአማካይ ከ100 ሺህ በላይ ተሳፋሪዎችን በደርሶ መልስ በማገልገል ላይ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም