በኢትዮጵያ የቼስ ስፖርትን ለማሳደግ ታዳጊዎች ላይ መስራት ይገባል- ናይጅል ሾርት

69
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010 የቼስ ስፖርትን ለማሳደግ የማሰልጠኛ ማዕከላትን በማቋቋም ታዳጊዎች ላይ መስራት እንደሚገባ እንግሊዛዊው የቼስ ግራንድ ማስተር ናይጅል ሾርት ገለጸ። የቼስ ግራንድ ማስተርነት የዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን (ፊዴ) የቼስ ተወዳዳሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያስመዘግቡት ውጤትና በሚኖራቸው ስፖርታዊ ጨዋነት የሚሰጣቸው ከፍተኛ ማዕረግ ነው። ለሁለት ቀን ጉብኝት ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ የገባው እንግሊዛዊው የቼስ ግራንድ ማስተር ናይጅል ሾርት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቆይታ አድርጓል። ናይጅል ሾርት የቼስ ስፖርት በኢትዮጵያ ላለፉት አምስት መቶ ዓመታት የቆየና ረጅም ታሪክ ያለው መሆኑን እንደሚያውቅ ለኢዜአ ገልጿል። ስፖርቱ በኢትዮጵያ ያሰቆጠረው ዘመን በአፍሪካ ስፖርቱ በዋንኛነት እየተዘወተረባቸው ካሉ አገሮች መካከል የሚጠቀስ እንደሆነ አንስተዋል። ያም ቢሆን ስፖርቱ በአገሪቷ እንዳለው ቆይታ ያለው እድገትና የውድድር መጠን አነስተኛ እንደሆነ ተናግሯል። በኢትዮጵያ የቼስ ስፖርትን ማሰልጠኛ ማዕከላትን በመገንባትና ታዳጊዎችን በማሰልጠንና በማስተማር በዘላቂነት ስፖርቱን ማሳደግ እንደሚቻልም አመልክተዋል። በቼስ ስፖርት ውጤታማ የሆኑ አገሮች ትልቁ የስኬታቸው ምስጢር ከታች ጀምሮ አካዳሚዎችን በመክፈት "ብቁና ክህሎት ያላቸው ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት የሚሰሩት ስራ እንደሆነና ኢትዮጵያ ከዚሁ ተሞክሮ መውሰድ ትችላለች" ብለዋል። በተጨማሪም ስፖርቱ እንዲያድግ የቼስ ተወዳዳሪዎች በዞን፣ በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ በስፖርቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍና ስፖንሰር በማፈላለግ የፋይናንስ አቅም ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል። የመንግስት ድጋፍ ለስፖርቱ እድገት ወሳኝና አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል። ስፖንሰር የማፈላለግ ጉዳይ ቀላል ባይሆንም በስፖርት ውስጥ ያሉ አመራር አባላት ትኩረት ሰጥተው መስራት ያለባቸው ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀዋል። የቼስ ስፖርት እንደ ሌሎቹ ስፖርቶች ብዙ የፋይናንስ ወጪ የማይፈልግና ቦታ የማይወሰድ በመሆኑ በቀላሉ ስፖርቱን ለማሳደግ እንደሚቻል ነው ናይጄል ሾርት የገለጸው። በአፍሪካ ባለፉት ዓመታት በውድድርና ብቃት ባላቸው ተወዳዳሪዎች የተሻለ እምርታ እያሳየች መምጣቷንም ተናግረዋል። እስካሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ 22 ጉብኝት ማድረጋቸውን የገለጹት ሾርት፤ በአህጉሪቷ ያለው የስፖርቱ እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ አመልክተዋል። የዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን(ፊዴ) እ.አ.አ በ1924 ከተቋቋመ ሀምሳ ዓመት በኋላ በአፍሪካ የመጀመሪያ ውድድር መካሄዱን አስታውሰው፤ ይህ ስፖርቱ በአፍሪካ ያለውን እድገት በሚፈለገው መልኩ እንዳይሆን እንዳደረገው አስረድተዋል። የቼስ ስፖርት ከውድድሩ ባለፈ የአዕምሮን የማመዛንና ውሳኔ ሰጪነት የሚያሳድግ እንደሆነ አስታውቀዋል። በመስከረም 2011 ዓ.ም በሚካሄደው የዓለም የቼስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት እጩ ሆነው የሚወዳደሩት ናይጅል ሾርት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ የቼስ ስፖርት ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሁም የፋይናንስ አስተዳደር ስርአቱ እንዲያድግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ናይጅል ሾርት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ከነበራቸው ቆይታ በተጨማሪ በቦሌ 19 የቼስ ክለብ በመገኘት ለቼስ ስፖርት አሰልጣኞች፣ዳኞችና ተጫዋቾች ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን አካፍለዋል። እንግሊዛዊው የቼስ ግራንድ ማስተር ናይጅል ሾርት ከኢትዮጵያ በመቀጠል ወደ  ኡጋንዳ እንደሚያቀኑ ለማወቅ ተችሏል። የናይጅል ሾርት ጉብኝት ኢትዮጵያ ከካስፓሮቭ የቼስ ፋውንዴሽን ጋር ባላት ግንኙነት መሰረት ፋውንዴሽኑ ያዘጋጀው እንደሆነም ተገልጿል። የ52 ዓመቱ ናይጅል ሾርት የቼስ ግራንድ ማስተርነት ያገኘው በ19 ዓመቱ እ.አ.አ በ1984 ነው። ከቼስ ግራንድ ማስተርነቱ በተጨማሪ የቼስ ስፖርት አሰልጣኝ፣ በእንግሊዝ በሚገኙ ጋዜጦች የቼስ ስፖርት አምደኛና የቼስ ስፖርት ውድድሮች ዘጋቢ ሆኖ ይሰራል። የዓለም አቀፉ የቼስ ፈዴሬሽን እስካሁን ለ1ሺ500 የቼስ ስፖርተኞች የግራንድ ማስተርነት ማዕረግ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም