ከገጠር ወደከተማ የሚደረገው ፍልሰት በአዲስ አበባ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ከመፍጠር ባለፈ ገጽታዋንም እያበላሸ ነው ተባለ

89
አዲስ አበባ ህዳር 8/2011 ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ተመጣጣኝ ያልሆነ ፍልሰት በሚፈጥረው ችግር አዲስ አበባ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ከመጋለጧ አልፎ ገፅታዋንም እያበላሸ መሆኑ ተገለፀ። ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት በከተማዋ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱም ተጠቁሟል። በኢትዮጵያ ከከተማ ወደ ገጠር ከሚደረገው ይልቅ ከገጠር ወደ ከተማ  የሚደረገው ፍልሰት አብዛኛውን እጅ ይይዛል። በኢትዮጵያ ፕላን ኮሚሽን የስነ-ህዝብና ልማት አስተባባሪ አቶ ፍቅሬ ገሶ ለኢዜአ እንዳሉት፤ እንዲህ አይነቱ ፍልሰት በበዛ ቁጥር ፍልሰቱ በሚካሄድበት ቦታ የማህበራዊ አገልግሎቶች እጥረት፣ የወንጀል መበራከትና ስራ አጥነት በስፋት ይስተዋላል። ፈልሶ ወደ ከተማ የሚገባው ህዝብ በከተሞች በቂ ስራ የማያገኝ ከሆነ ወደ ዘረፋ የሚሰማራባት ዕድል ሰፊ መሆኑንም ጠቁመዋል። ለፍልሰት የሚዳርጉ ሳቢና ገፊ የሚባሉ ሁለት ምክንያቶች ያሉ ሲሆን እነዚህም ከመሰረተ ልማት መስፋፋት፣ ከተፈጥሯዊ ሁኔታና ከደህንነት ጋር እንደሚያያዙም ነው የሚገልፁት። ሳቢ የሚባለው ሰዎች የተሻለ ነገር ፍለጋ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የሚፈልሱበት ሲሆን ገፊ የሚባለው ደግሞ በተለያየ ምክንያት የሚፈናቀሉበት አስገዳጅ ሁኔታ ሲያጋጥም ነው። በፍልሰት መነሻ ቦታዎች የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የማህበራዊ አገልግሎቶች አለመሟላት፣ ደጋፊ ማጣትና መሰል ጉዳዮች እንደምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ሁለተኛውና ሶስተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ እንደሚያሳየው አዲስ አበባ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልል ከተሞች ከፍተኛ ፍልሰት የሚስተናገድባቸው መሆኑን ያሳያል። አዲስ አበባ ደግሞ የችግሩ ሰፊ ማሳያ መሆኗን አቶ ፍቅሬ ያስረዳሉ። በ2007 በተካሄደ ጥናትም ይሄ ቁጥር በአዲስ አበባ ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን አቶ ፍቅሬ ተናግረዋል። በዚህም ሳቢያ ከተማዋ የማህበራዊ አገልግሎቶችን በተሟላ መልኩ እንዳታደርስ ከማድረጉም ሌላ በጎዳና ላይ የሚታየው ኑሮ የከተማዋን ገፅታ እያበላሸው እንደሆነ አስታውቀዋል። ይህን ችግር ለመፍታት መንግስት በሁሉም አካባቢ ተመጣጣኝ የሆነ የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ማቅረብ እንዳለበት ይመክራሉ። የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘውዴ ቀፀላ በበኩላቸው አዲስ አበባ ላይ እየተበራከተ የመጣው ፍልሰት በነዋሪው ላይ ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ አመልክተዋል። አሁን ያለውን ችግር በመረዳት እዚህ ያሉትን መልሶ ለማቋቋምና አዲስም ወደከተማዋ እንዳይገባ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ይናገራሉ። በተጨማሪም ከክልል ወደአዲስ አበባ የሚመጡ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችና እንግልቶች እንደሚዳረጉም በማንሳት። በፍልሰት ወደከተማዋ የሚመጡት ከክልሎች በመሆኑ ጉዳዩ በአዲስ አበባ አስተዳደር ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን ገልፀዋል።   ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅና ያሉትንም ለማቋቋምና ወደቤተሰቦቻቸውም ለመመለስ ከክልሎች ጋር ለመስራት በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም