አክቲቪስት ጃዋርና የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ከአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ

66
አሶሳ ህዳር 8/2011 አክቲቪስት ጃዋር መሐመድና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ /ኦፌኮ/ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ  በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ከአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ፡፡ በውይይቱ ወቅት አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ እንዳለው ካድሬዎች ስልጣን ላይ ቁጭ ብለው ህዝብን እያጣሉ ሃገርን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል፡፡ " ኢትዮጵያ በርካታ የተማሩ ልጆች አሏት " ያለው ጃዋር  ከህዝብ ጋር አብረው በመታገል ጨካኙን አገዛዝ ላይመለስ እንዲወገድ ማድረጋቸውን ተናግሯል፡፡ ዜጎች ከመቼውም በበለጠ ሃገራቸውን ነቅተው መጠበቅ እንደጀመሩ ገልጾ " ከእግዲህ በሀገሪቱ አምባገነን ስርዓት ፈጽሞ አያንሰራራም በአዲስ መልክም አይወለድም " ሲል ለውይይቱ ተሳታፊዎች አስረድቷል፡፡ ህብረተሰቡ የትኛውንም የመንግስት አመራር ያለበቂ መረጃ አለአግባብ መውቀስ እንደማይገባም መክሯል፡፡ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው በሀገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ለሚከሰቱ ግጭቶች የመንግስት ሀገርን የማስተዳዳር አቅም ክፍተት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ደግሞ በየአካባቢ ተዘዋውረው ህዝቡን ባወያዩበት ወቅት አመራሩ በራስ መተማመን ውሳኔ ለመስጠት ሲቸገሩ መመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡ "ለለውጡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ታግሏል" ያሉት አቶ በቀለ እስከመጪው ምርጫ አሁን ያለውን መንግስትን በሚገባ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊ ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ለውጡ ቀጣይነት የሚኖረው በዘር በቀለም ተለያይቶ የሚደረገው ግጭት ሲቆም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንገድ መዝጋት ለዜጎችን ሆነ ለሀገር እንደማይጠቅም የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ ለመፍትሔው የውይይት መድረኩን የመሩት ከህዝብና መንግስት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በተከሰተው ግጭት ህብረተሰቡ ለችግር እየተዳረገ እንደሆነ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝና ለዘመናት አብረው የኖሩ የአካባቢውን ማህበረሰብ አንድነት ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ አቶ ጃዋር መሃመድ" ከአሶሳ፣ ከሶማሌ እና ከትግራይ ክልል ከተሞች ወደ አዲስ አበባ መንገድ በተደጋጋሚ መዘጋቱን ዜጎች በነጻነት ለመንቀሳቀስ መቸገራውን አውቃለሁ "ብሏል፡፡ የመንገድ መዘጋትን ጨምሮ በየክልሎች አስቸኳይ ውይይት ተደርጎባቸው ሊፈቱ የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን  ጠቅሷል፡፡ ይህም የፌዴራል ስርዓቱ እና የሃገሪቱን ኢኮኖሚ አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ግለሰቦች ብሄርን መሰረት አድረጎ የሚሰነዘር ጥቃት ከወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ጋር የማይሄድ አሳፋሪ በመሆኑ  ይህን የሚፈጽሙ በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባም ጠቋሟል፡፡ አክቲቪስቱ " ህብረተሰቡ ጥርጣሬን በማስወገድ እና እርስ በርስ በመተማመን ከግጭት ትርፍ ሊያጋብሱ የሚሯሯጡ ሌቦችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም ይገባል " ብሏል፡፡ ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ጭምር ሲያደረገው የነበረውን ሰብዓዊ መብት የማስከበር ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ በውይይት መድረኩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ጨምሮ ሁለት ሺህ የሚጠጉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም