የእንቦጭ አረም ለሐይቆችና ውሃማ አካላት ከፍተኛ ስጋት ሆኗል

123
ህዳር 8/2011 የእንቦጭ አረም የጣና ሃይቅን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ሐይቆችና ውሃማ አካላት ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መምጣቱን የአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ፡፡ በኮሚሽኑ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ የደህንነት፣ ህይወትና ወራሪ መጤ ዝርዎች ዳይሬክቶሬት ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኤርሚያስ ማስረሻ  እንዳሉት የእምቦጭና ሌሎች የመጤ ወራሪ እጽዋት በስነምህዳር ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው። ይሄን መነሻ በማድረግም በኮሚሽኑ  ችግሩን በቅርበት የሚከታተል የደህንነት፣ ህይወትና ወራሪ መጤ እጽዋት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬትን ከስድስት ወርበፊት በአዲስ መልክ ማቋቋሙንም ተናግረዋል። የጣና ሐይቅን ጨምሮ የእንቦጭ አረም  ከታየባቸው ሐይቆችና ወንዞች መካከል አባያ ሐይቅ፣ ዝዋይ ሐይቅ፣ የቆቃ ግድብና የባሮ ወንዝ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ በ2003 ዓ.ም ሲከሰት 50ሺ ሄክታር ሸፍኖ እንደነበር የገለፁት  አቶ ኤርሚያስ የአካባቢው ህብረተሰብ ባደረገው ጥረት 2008 ዓ.ም ወደ 20ሺ ሄክታር ዝቅ  ማድረግ ተችሎ ነበር በተከታተይ የአካባቢው ህብረተሰብና ሌሎች አካላት በተደረገ ጥረት ባለፈው ግንቦት ወደ  5ሺ 936 ሄክታር ዝቅ ቢልም ዛሬ ላይ ችግሩ ተባብሶ 80 ሺህ ሄክታር መድረሱን ነው ባለሙያው የሚናገሩት፡፡ ሁለት ማሽኖች ከዲያስፖራው በተዋጣው ገንዘብ ተገዝተው ወደ ስራ ቢገቡም የቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ብዙም ሳይሰሩ እንደቆሙና በቶሎ  ማስጠገን ባለመቻሉ  በሰው ጉልበት ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት የችግሩ ስፋት አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል። ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ያለመስራት ክፍተት መኖሩ ችግሩን በሚፈለገው ልክ መከላከል እንዳልተቻለም ነው አቶ ኤርሚያስ ያስረዱት። በተለይ አባያ ሀይቅ አዞዎች፣ ዘንዶና ጉማሬዎች ስላሉ በሰው ጉልበት ለማስወገድ አስቸጋሪ  ቢሆንም ከተወረረው ከ1 ሺ 700 ሄክታር የሃይቁ አካል ህብተሰቡ ማደረገው  ጥረት 4 ሔክታር ብቻ ማስወገድ እንተቻለ ነው የተገለፀው። ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ እንቦጭን ብቻ መመገብ የሚችሉ 4ሺ ጥንዚዛዎች በላብራቶሪ ማምረቱን የጠቆሙት ባለሙያው 2ሺ የሚሆኑት ወደ ሥፍራው ለማብረር ዝግጁ መሆናቸውንና  በቅርቡ ወደ ተግባር ይገባል ብለዋል። ባለፈው መስከረም የባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ከዘርፉ ባለ ሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶ ከአለምአቀፍ ተቋም  ለዚሁ ተግባር የሚውል ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ  ለማድረግ ቃል መግባቱንም ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላትጋር ሆኖ በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን በመቀመር ወራሪና መጤ ዝርያዎችን መቆጣጠር የሚቻልበት ፖሊሲ እያዘጋጀ መሆኑን የገለፁት ባለሙያው  በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋልም ብለዋል። ወራሪ መጤ የእጽዋት ዝርዎች በማወቅና ባለማወቅ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ሃገር ወስጥ   እንደገቡም ነው ባለሙያው ያብራሩት፡፡ ኮሚሽኑ ባለፈው አመት ለዚህ ተግባር የሚውል 2.5 ሚሊየን ብርን ጨምሮ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ መነሻው ላቲን አሜሪካ እንደሆነ የሚነገረው የእንቦጭ አረም  በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ  በ1956 ዓ.ም አቡነ ሳሙኤል ግድብ መታየቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ከ35 በላይ ወራሪ  መጤ እጽዋት መኖራቸውንም ከከሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም