የመስኖ ልማት ስራ ሀብት ማፍራት አስችሎናል---የጅማ ራሬ ወረዳ አርሶ አደሮች።

60
ነቀምቴ ህዳር 8/2011 በመስኖ ልማት ስራ መሰማራታቸው ሀብት ማፍራት እንዳስቻላቸው አንዳንድ ጅማ ራሬ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች ገለጹ። በዞኑ ከ52 ሺህ 900 ሄክታር መሬት በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል። አርሶ አደር ተሾመ ወርቁ በጅማ ራሬ ወረዳ የኢብሳ ኢላሙ ቀበሌ  ነዋሪ  ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ዝናብ ጠብቀው የሚያመርቱት ምርት ከእጅ ወደ አፍ እንደነበር ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመስኖ ልማት ስራ በመሰማራታቸው ተጨባጭ ውጤት እያገኙና በኑሯቸውም እየተለወጡ  መሆኑን  ገልጸዋል፡፡ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ከመኸር እርሻ በተጓዳኝ  የመስኖ ልማት ስራ እንደጀመሩ ያስታወሱት አርሶ አደሩ በአንድ የምርት ወቅት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ከሚለሙት መሬት ምርት ሽያጭ እስከ 20 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉተ ካገኙት ገቢም ሁለት የእርሻ በሬዎችን  ከመግዛት አልፈው ደሳሳ የሳር ጎጇቸውን ወደ ቆርቆሮ ቤት መቀየር ችለዋል፡፡ በወረዳው የሰቶሳ ገመቸስ ቀበሌ አርሶ አደር እራሱ ደርጩ ከዚህ ቀደም እሳቸውን ጨምሮ የቀበሌው አርሶ አደሮች ስለመስኖ ልማት ስራ ግንዛቤ ስላልነበራቸው  የልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በግብርና ባለሙያዎች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ከቀበሌው አርሶ አደሮች ጋር በልማት ቡድን በመደራጀት በመስኖ ልማት ስራ በመሰማራታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የክረምት ዝናብን ጠብቀው የሚያመርቱት ሰብል ከ5 እስከ 10 ኩንታል ምርት ያገኙ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሩ በአሁኑ ሰዓት መስኖን በመጠቀም ቲማትም፣ ድንች፣ ቃርያ እና ጥቅል ጎመን በማሳቸው በማምረት በዓመት እስከ 30 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውን ኑሮ መለወጥ መቻላቸውን አመልክተዋል፡፡፡ በመስኖ ልማት ስራ ባገኙት ተጨማሪ ገቢም  በጅማ ራሬ ወረዳ ባለ አምስት ክፍል ቤት ከመግዛት ባለፈ በሚኖርበት ቀበሌ ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት መስራት እንደቻሉም ጠቁመዋል፡፡ በግለሰብ ቤት ተቀጥረው የእርሻ ስራ ይሰሩ እንደነበር የተናገሩት ሌላው የቀበሌው አርሶ አደር ፈቃዱ ጨምደሳ "በአሁኑ ሰዓት በመስኖ ልማት ስራ በመሰማራቴ ተጠቃሚ ሆኛለሁ" ብለዋል፡፡ የዞኑ የመስኖ ባለስልጣን የኤክስቴንሽን ባለሙያ አቶ ደረጀ ኦልጅራ እንዳሉት በተያዘው ዓመት ዘመናዊና ባህላዊ የመስኖ አውታረን በመጠቀም በሁለት ዙሮች 52 ሺህ 934 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ነው። እስካሁንም ከ8 ሺህ 100 ሄከታር መሬት በላይ በመስኖ መልማቱን ያስታወቁት ባለሙያ በአጠቃላይ ከሚለማውም 6ሚሊዮን 700ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። በልማቱም ከ144 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ለማሳተፍ ታቅዷል፡፡ የሚጠበቀው ምርት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ184 ሺህ 400 ኩንታል ብልጫ እንደሚኖረው ባለሙያው አመልክተዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም