ፖሊስ ተሽከርካሪን አግቶ የሰው ህይወት እንዳጠፋ የጠረጠረውን ግለሰብ መያዙን አስታወቀ

78
ፍቼ ህዳር 7/2011 በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን የወረጃርሶ ወረዳ ፖሊስ ተሽከርካሪን በማገት የሰው ህይወት አጥፍቷል  ተብሎ የተጠረጠረ ግለሰብን  መያዙን አስታወቀ፡፡ የወረዳው ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር መንግስቱ አየለ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቡ  ከጉሀ ጽዮን ወደ አማራ ክልል ደጀን የሚሄዱ 12 ሰዎች አሉ ብሎ ገብረጉራቻ  ከተማ ላይ  ከአንድ ሀይ ሩፍ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪ ጋር በ5ሺህ ብር ኮንትራት ይዋዋላሉ፡፡ ከዚያም ጎሀ ጽዮን ከተማ ከደረሱ በኋላ አሽከርካሪው ለተዋዋለው ግለሰብ  ተሳፋሪዎቹ የታሉ ብሎ ሲጠይቀው ከመንገዱ ወጣ ብለው እንደሚገኙ ይነግረዋል፡፡ አሽከርካሪውና ረዳቱ  ከዋናው መንገድ አንወጣም ብለው ሲከራከሩ ግለሰቡ ሽጉጥ ያወጣና አብሯቸው የነበረው የተሽከርካሪው ባለቤት ዘመድ ሽጉጡን ለማስጣል ሲሞክር ተኩሶ ይገድለዋል፡፡ ከዚያም ረዳቱ ሁኔታውን ለወረ ጃርሶ ወረዳ ፖሊስ ሪፖርት ማድረጉን ኢንስፔክተር  መንግስቱ ገልጸዋል፡፡ ኢንስፔክተሩ እንዳሉት የወረዳው ፖሊስም ከአማራ ክልል ፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ ተጠርጣሪው ግለሰብ ደጀን ወረዳ ጉባ በተባለው አካባቢ ይያዛል፡፡ ሟቹ የገብረ ጉራቻ ከተማ ነዋሪ በመሆኑ ዛሬ የቀብር ስነስርዓቱ ለመፈጸም ብዛት ያለው የከተማው ነዋሪ ህዝብ አስክሬኑን ይዞ ወደ ቀብር ቦታው ለመድረስ በዋናው የመኪና መንገድ ሲጓዝ መንገዱ ለተወሰነ ጊዜ ለተሽከርካሪ ተዘግቶ  እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ፖሊስ ከህብረሰተቡ ጋር ተነጋገሮ መንገዱ ወዲያው መከፈቱንና የተሽከርካሪ ምልልሱ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡ በተጠርጣሪነት ከተያዘው ግለሰብ ጋር የነበሩ ሌሎችም ተባባሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ኢንስፔክተሩ አብራርተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም