አፍሪካ የሰላም ፈንድ መዋጮን ተግባራዊ እያደረገች ነው

119
አዲስ አበባ ህዳር7/2011 የአፍሪካ ህብረት ለሰላም ፈንድ የሚውል 55 ሚሊዮን ዶላር ከአባል አገራቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መሰብሰቡን አስታወቀ። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አባል አገራቱ የህብረቱን የፋይናንስ ሪፎርም በመተግበር ሂደት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል። አፍሪካ በአህጉሪቷ የሚከሰቱ ግጭቶችን በራስ አቅም ለመፍታት ይቻላት ዘንድ ከ2017 ጀምሮ የሰላም ፈንድ ተግባራዊ እያደረገች ሲሆን፤ ፈንዱ ከአባል አገራቱ በየዓመቱ 65 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ውጥን አስቀምጧል። ይህ እውን ይሆን ዘንድም በሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ መሪነት ህብረቱ እየተገበራቸው ካሉ ተቋማዊ የለውጥ ስራዎች መካከል ከአባል አገራቱ የሚሰበሰብ የ0 ነጥብ 2 በመቶ የገቢ ታክስ መዋጮ ተጠቃሽ ነው። የተቋማዊ ለውጥ ቡድን ኃላፊ የሆኑት ፕሮፈሰር ፔር ሞኮኮ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ አባል አገራቱ እስካሁን ባለው ሂደት በአንድ ዓመት ውስጥ 55 ሚሊዮን ዶላር አስተዋጽኦ አድርገዋል። ይህም እጅግ የሚደነቅ ቁርጠኝነት መሆኑን ነው ኃላፊው የተናገሩት።  አባል አገራቱ ህብረቱን በራሱ በፋይናንስ ለማስቻል የተቀመጠውን ሪፎርም በመተግበር ረገድም ጥሩ ሂደት ላይ መሆናቸውንም አውስተዋል። ሃያ አራት የሚሆኑ የህብረቱ አባል አገራት የፋይናንስ ሪፎርሙን ለመተግበር በሂደት ላይ መሆናቸውንም ለአብነት አንስተዋል።  እንደ ፕሮፌሰር ፔር ሞኮኮ ገለጻ፤ የመካከለኛውና የምእራብ አፍሪካ አገራት የገቢ ታክስ ሪፎርሙን በመተግበር ረገድ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ነገ የሚጀመረው የህብረቱ 11ኛው ልዩ የመሪዎች ስብሰባም ይህንና መሰል ተቋማዊ ለውጦችን ቶሎ ውጤታማ የሚያደርግ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም