በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ እንዲጠናከር ለሴቶች የተሰጠው ኃላፊነት የጎላ ሚና ይኖረዋል-የሊጉ ሊቀመንበር

68
ባህርዳር ህዳር 7/2011 ሴቶች በብቃታቸውና በችሎታቸው እኩል የስልጣን ዕርከን መያዛቸው በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ እንዲጠናከር የጎላ ሚና እንደሚኖረው  የአዴፓ ሴቶች ሊግ ሊቀመንበር ተናገሩ። " የለውጡ ቀጣይነት ለዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ለሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት " በሚል መሪ ሀሳብ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሴቶች ሊግ አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ማምሻውን በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል። ሊቀመንበሯ ወይዘሮ ውብዓለም በዚህ ወቅት እንዳሉት ሴቶች አቅማቸውንና የመወሰን ችሎታቸውን እያሻሻሉ መጥተዋል። በዚህም በፌዴራል መንግስቱ ከፍተኛ የስልጣን ዕርከን እኩል የሚሆነውን የካቢኔ ቦታ እንዲይዙ መደረጉ ሀገሪቱ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንድትሆን እንዳስቻላትም ተናግረዋል። " የአዴፓ ሴቶች ሊግም በክልሉ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ  ተሳታፊነትና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ እየሰራ ይገኛል" ብለዋል። አሁን የተገኘውን ለውጥም ከዳር ለማድረስና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል። ሴቶች በብቃታቸውና በችሎታቸው እኩል የስልጣን ዕርከን መያዛቸው ሀገራዊ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚኖራቸው ሚና የጎላ መሆኑን የሊጉ  ሊቀመንበር አስታውቀዋል። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ በበኩላቸው በሀገሪቱ በመጣው የለውጥ ጉዞ የሴቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። " የተገኘው የለውጥ ጉዞ ስቃይ የበዛበት ነው፤  የተደላደለ ሀገር ለመገንባትና ለውጡ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አቅም ያላቸው ሴቶች ይፈለጋሉ" ብለዋል። አቅም ያላቸውና የበቁ ሴቶችን ከያሉበት በማውጣት ወደመሪነት ቦታ እንዲመጡ የማድረጉ ስራ ደግሞ የአዴፓ ሴቶች ሊግ ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ለውጡን ተከትሎም በየአካባቢው እየተስተዋለ ያለው የህግ ጥሰት እንዲከበርና ዴሞክራሲ እንዲያብብ ሊጉ ከመቼውም ጊዜ በላቀ  ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል። የሊጉ መደበኛ ጉባኤ  ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚያደርገው ቆይታ  በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡ በጉባኤው መክፈቻ ስነስርዓት   የድሬዳዋና የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደሮች፣ የደቡብ እና  የኢህ አዴግ ሴቶች ሊጎች ተገኝተው የአጋርነት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም