በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአትሌቶች ላይ የአበረታች ቅመም ምርምራ ይካሄዳል

66
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ በሚካሄደው የታላቁ ሩጫ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በአትሌቶች ላይ የአበረታች ቅመም ምርምራ እንደሚካሄድ ተገለጸ። የኤርትራው ታዋቂ አትሌት ዘረሰናይ ታደሰና ዩጋንዳዊው የማራቶን ሯጭ ስቴቨን ኪፕሮቲች በውድድሩ ቀን በክብር እንግድነት ይገኛሉ። ከነገ በስቲያ የሚካሄደውን ውድድር አስመልክቶ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል። ውድድሩም "ቀጣይ መሪ የሚሆኑ ሴት ልጆችን አሁን እናብቃ" በሚል መሪ ሀሳብ  እንደሚካሄድም ተጠቁሟል። ከመላው ዓለም የሚመጡትን ጨምሮ በጠቅላላው 44 ሺህ ህዝብ ይሳተፍበታል ተብሎ የሚጠበቀው የዘንድሮውን ሩጫ መነሻና መድረሻ ቦታ ስድስት ኪሎ የሚገኘው የሰማእታት ሀውልት ነው። በዚህም መሰረት ሩጫው ከአደባባዩ በመነሳት በሚኒሊክ ሆስፒታል፣ እንግሊዝ ኤምባሲ በኩል ሾላ ገበያን በመዞር በአድዋ ድልድይ አድርጎ አራት ኪሎ ፓርላማን በማቋረጥ ስደስት ኪሎ ሰማእታት ሀውልት ያበቃል። ከዚህ በፊት የውድድሩ መነሻና መድረሻ መስቀል አደባባይ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ውድድሩ ይካሄዳል ተብሎ በተያዘበት ቀን ከአፍሪካ ህብረት ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ጋር በመገጣጠሙ ቦታው እንዲቀየር መደረጉን የውድድሩ አዘጋጆች ከሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ መግለጻቸው ይታወቃል። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤሚያስ አየለ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በእሁዱ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በአትሌቶች ላይ የአበረታች ቅመም ምርመራ ይካሄዳል። ምርምራው የሚካሄደው ከኢትዮጵያ ፀረ- አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር መሆኑንና በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ 7 ሺህ አትሌቶች ላይ  የአበረታች ቅመም ምርመራ እንደሚካሄድ ገልጸዋል። ይህም ያስፈለገው በአሁኑ ሰአት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአትሌቲክሱ የአበረታች ቅመም መጠቀም ችግር አንገብጋቢ እየሆነ በመምጣቱና ችግሩን ለመከላከል በማስፈለጉ እንደሆነ ጠቅሰዋል። አትሌቶች የሚያገኙት ውጤት የሚጸድቀውም በአበረታች ቅመም ምርመራው ላይ በተገኘው ውጤት አማካኝነት እንደሆነም አመልክተዋል። ካለፉት 17 ውድድሮች በተሻለ መልኩ ከኤርትራ፣ዩጋንዳ፣ኬንያና ቦትስዋና የተወጣጡ 13 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ይህም በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ የጎረቤት አገራት አትሌቶች የሚሳተፉበት እንደሆነም ነው አቶ ኤርሚያስ ያስረዱት። አትሌቶቹን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ 500 ሯጮች በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል። ከአጠቃላዩ 44ሺህ ተሳታፊ 7ሺው ሯጮቹ አረንጓዴ ቲሸርት የሚለብሱ ሲሆን ቀሪው 37 ሺህ ቀይ ቲሸርት እንደሚለብሱም ጠቅሰዋል። የመሮጫ ቁጥር እያንዳንዱ ባር ኮድ ሲኖረው ማንኛውም ተሳታፊ ያለ መሮጫ ቁጥር ለመሳተፍ ቢሞክር ከውድድሩ ውጪ እንደሚሆን አስገንዝበዋል። 3 ሺህ ህጻናት የሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር ነገ ከጠዋቱ 3 ሰዓት በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ እንደሚካሄድም አክለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም