የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ለሰላም ትኩረት መስጠት ይገባል- ታዋቂ ግለሰቦች

67
አሶሳ ህዳር 7/2011 በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ሕዝቡ ለአካባቢው ሰላም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ሁለት ታዋቂ ግለሰቦች አሳሰቡ። አክቲቪስት ጃዋር መሐመድና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ(ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ ከአሶሳ ከተማው ነዋሪዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት እንዳስገነዘቡት ሕዝቡ የለውጡን ቀጣይ ለማረጋገጥ  ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት፡፡ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን መፍታት ለለውጡ ቀጣይነት ወሳኝነት እንዳለውም አመልክተዋል። በሁለቱ ወንድማማችና ተጎራባች ሕዝቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች መንስዔዎችን በመረዳት የፌዴራልና የክልሉ መንግሥታት መፍትሄ እንዲሰጧቸው ለማድረግ ውይይቱ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተፈጠሩ ችግሮችን በውይይት ይፈታሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ለውጡን ለማደናቀፍና በሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ አካላትን ድርጊት ለማስቆም አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡ ለኦሮሞ ሕዝብ መብትና ጥቅም መከበር እንታገላለን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ለመሥራት በዚህ ሳምንት የደረሱት ስምምነት አስደስቶናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም