በድሬዳዋ አስተዳደር የገጠር ንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እየተገነባ ነው

56
ድሬዳዋ/ነቀምቴ ህዳር 7/2011 በድሬዳዋ አስተዳደር ገጠር አካባቢ ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል ከ32 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የአስተዳደሩ ውሃ ፣መስኖና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ በምሥራቅ ወለጋ ደግሞ ሳይጠናቀቁ የቀሩ ጨምሮ 28 የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ  ሊካሄድ ነው፡፡ የድሬደዋ አስተዳደር የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ገረመው ለኢዜአ እንደተናገሩት የ"ዋሽ" ፕሮጀክትና አስተዳደሩ በመደቡት በጀት  ባለፈው ሐምሌ ወር የተጀመረው የውሃ ፕሮጀክት የለገኦዳ ገጠር ቀበሌ ነዋሪን የዓመታት የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው፡፡ 20 በመቶ ግንባታው የተጠናቀቀው ፕሮጀክት በሚቀጥለው ሰኔ ወር ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ይጠበቃል፡፡ በድሬዳዋ የ" ዋሽ" ፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ ባለሙያ    አቶ መብራቴ ጌታሁን በበኩላቸው "በለገኦዳ ከተጀመሩት 28 የቦኖ ውሃ ግንባታዎች 22 ተጠናቀዋል፤ ከ50 እስከ 200 ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ የሚችሉ ስድስት የውሃ ማጠራቀሚያዎች እየተገነቡ " ነው፡፡ ጥልቅ የውሀ ጉድጓድ መቆፈሩንና ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ የቧንቧ  መስመር ዝርጋታ በየመንደሩ እንደሚዘረጋ ተናግረዋል፡፡ የተቆፈረው ጥልቅ ጉድጓድ በሰኮንድ 10 ሜትር ኪዮብ ውሃ ማመንጨት እንደሚችል ጠቅሰው ይህም ለ20 ዓመታት የነዋሪዎችንና የሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውሃ ጥያቄዎች መመለስ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ " ሴቶች ውሃ ፍለጋ ከአካባቢው ከአራት ሰዓት በላይ ይጓዛሉ፤ ይህ ደግሞ በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፤ የተጀመረው ፕሮጀክቶች በተለይ ለሴቶች ከፍተኛ ተስፋ ሰጥቷል" ያሉት ደግሞ  የለገኦዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ኑሪያ ሃሚዶ ናቸው፡፡ የቀበሌው ሊቀመንበር አቶ መሐመድ አብደላ መንግስት የህዝቡን የዓመታት የውሃ ችግር ጥያቄዎች በመፍታት የጀመረው ግንባታ በየደረጃው የሚገኘውን ህዝብ ያስደሰተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የአስተዳደሩ ክትትልና ድጋፍ ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡ ነዋሪው ለፕሮጀክቱ ዳር መድረስ የእርሻ መሬቱን በመተውና ተሳትፎውን በማጠናከር ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የቀበሌው ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ባህረዲን መሐመድ ነዋሪው እየተጠቀመ የሚገኘው ንፁህናው ያልተጠበቀ ውሃ ለተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች እየዳረገው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ " ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለችግራችን መፍትሄ ያመጣል፤ እስከዚያው ግን ህብረተሰቡ የሚጠጣውን ውሃ ንፅህናውን ጠብቆ  እንዲጠቀም እያስተማርን ነው"ብለዋል፡፡ ይህን በእንዲህ እንዳለ በምሥራቅ ወለጋ ሳይጠናቀቁ የቀሩትን ጨምሮ በተያዘው የበጀት ዓመት 28 የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ  እንደሚካሄድ የዞኑ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡ ግንባታው የክልሉ መንግሥት በመደበው ከ16 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሚካሄድ ነው፡፡ በዞኑ በሚገኙ 14 ወረዳዎች የሚገነቡ ፕሮጀክቶቹ  በሞተር ኃይል የሚሳቡ ምንጮችና ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች መሆናቸውን የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ አንዱዓለም አያኖ ገልጸዋል፡፡ ከፕሮጀክቶቹ መካከል 22ቱ   በ2006 ዓ.ም.ግንባታቸው ተጀምሮ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የሚያስፈለጉ ቁሳቁሶች በወቅቱ ባለመቅረባቸው ሲጎተቱ የቆዩ ሲሆኑ ቀሪዎቹ አዲስ የመጀመሩ ናቸው፡፡ የነባሮቹ ግንባታ በአብዛኛው በመገባደዳቸውና ለማጠናቀቂያ የሚስፈልጉ ቁሳቁሶች በመሟላታቸው በበጀት ዓመቱ ውስጥ አልቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ አቶ አንዱዓለም ተናግረዋል፡፡ አዲሶቹ ፕሮጀክቶች በመጪው ዓመት ለማጠናቀቅ የታቀዱ ሲሆን የሁሉም ግንባታ ለመጀመር በአሁኑ ወቅት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ እንዳመለከተ ፕሮጀክቶቹ  ሲጠናቀቁ  ከ77ሺህ ለሚበልጥ ህዝብ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋሉ፤ ዞኑን የውሃ ሽፋን አሁን ካለበት 65 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 76 በመቶ እንደሚያሳድጉት ይጠበቃል፡፡                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም