በባስኬቶና በመሎ ወረዳ መካከል በተከሰተው ግጭት ለጉዳት መዳረጋቸውን የመሎ ኮዛ ወረዳ ተወላጆች ገለጹ

78
ሀዋሳ ህዳር 7/2011 የማንነት ጥያቄን ተከትሎ በባስኬቶና በመሎ ወረዳ መካከል በተከሰተው ግጭት እየተጎዱ መሆናቸውን ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በትምህርትና በሥራ ላይ የተሰማሩ የመሎ ኮዛ ወረዳ ተወላጆች ገለጹ፡፡ በዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሞት እንዲቆምም ተወላጆቹ ጠይቀዋል፡፡ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት አቶ ማሩፋ መኩሪያ ችግሩን አስመልክተው እንደገለጹት በጥናት ያልተረጋገጠ መረጃ በመያዝና የማንነት ጥያቄ ያለ በማስመሰል በተከሰተው ግጭት የወረዳው አርሶ አደሮች ችግር ላይ ወድቀዋል፡፡ ሰሞኑን በተፈጠረው አለመረጋጋት የሰው ሕይወት መጥፋቱን አስታውሰው የዜጎች ሰብዓዊ መብትና የህግ የበላይነት እንዲከበር እንደሁም ሰላምና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ጠይቀዋል፡፡ "በተለያየ ሁኔታ ተደራጅተውና ታጥቀው ጉዳት እያደረሱ የሚገኙ አካላት ለህግ መቅረብ አለባቸው" ብለዋል፡፡ የወረዳው አርሶ አደር ከአካባቢው ተፈናቅሎ ለችግር እየተጋለጠ መሆኑን የገለጸችው ደግሞ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ጥሩሰው አብርሃም ናት፡፡ ግጭቱን ተከትሎ የባስኬቶ ወረዳን አቋርጦ የሚሄደው መንገድ በመዘጋቱ ከቤተሰቦቿ የሚደረግላት ድጋፍ መቋረጡንና ይህም በትምህርቷ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጻለች፡፡ በመሎ ኮዛ ወረዳ የላሃ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት አሰግድ አለማየሁ በበኩሉ ችግሩን እየፈጠሩ ያሉት መዋቅራዊ የመስፋፋት ጥያቄ ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን ጠቁሟል። በችግሩ ተጎጂ እየሆኑ መሆናቸውን የገለጸው ወጣት አሰገድ መንግስት ገንዘብ በማሰራጨት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ አካላትን ለመታደግ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቋል። "ጥያቄያችን የማንነትና የፖለቲካ ሳይሆን የአርሶ አደሩ በሕይወት የመኖርና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ እንዲከበሩ ነው" ሲል ተናግሯል፡፡ "ችግሩ መፈጠር ከጀመረ ስድስት ወራትን አስቆጥሯል" ያለው ወጣት አሰግድ ከሰላማጎ አራት ቀበሌያት የተፈናቀሉ ግለሰቦች በላሃ ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙና ሰብአዊ ድጋፍ አየተደረገላቸው አለመሆኑን ተናግሯል፡፡ በተመሳሳይ ዜና በአርባ ምንጭ ከተማና በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያሉ የጎፋ ተወላጅ የሆኑ የመንግስተ ሰራተኞችና ተማሪዎች በግጭቱ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በሰላማዊ ሰልፍ አውግዘዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዓመት የህግ ተማሪ ታረቀኝ ፀጋዬ እንደገለጸው በአካባዊው በግጭቱ እየተፈፀመ ያለውን ተግባር መንግስት እንዲያስቆም ጠይቋል፡፡ መሎ ኮዛ ወረዳ ከሳውላ፣ ወላይታ፣ አርባ ምንጭና ሌሎች አካባቢዎች ጋር የሚያገናኘው መንገድ መዘጋቱንም ተናግሯል፡፡ የመሎ ኮዛ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ጌታቸው ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ስድስት ወራትን ያስቆጠረ ግጭት በባስኬቶ ልዩ ወረዳና በመሎ ኮዛ ወረዳ መካከል መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት መሎ ኮዛ  ወረዳን ከአርባ ምንጭና ከሶዶ አዲስ አበባ የሚያገናኙ መንገዶች ዝግ መሆናቸው የወረዳው ህዝብ ህክምናን ጨምሮ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ከወረዳው ውጭ ለማግኘት እንቅፋት እንደሆነበት አስታውቀዋል፡፡ "ጥቃቱ በተቀናጀና በታጠቁ ኃይሎች የተፈጸመ ነው" ያሉት አስተዳዳሪው እስካሁን በግጭቱ ምክንያት ስምንት ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸውና ከቄያቸው ተፈናቅለው በመሎ ኮዛ ወረዳ ማዕከል በሆነችው ላሃ ከተማ፣ ገርገዳና ባዛር ቀበሌዎች መጠለላቸውን ገልጸዋል፡፡ በታጠቁ ቡድኖች 21 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው የማንነት ጥያቄ አለብን የሚሉ አካላት አስካሁን ለወረዳው መንግስት ቅሬታም ሆነ አቤቱታ አለማቅረባቸውን አቶ ጥላሁን ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡ የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አርኮ ደምሴ በበኩላቸው በአካባቢው ላይ በተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱንና በርካቶች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል ፡፡ "የዞኑ መንግስት ከክልሉ ፀጥታ አስተዳደር ጋር በመሆን ህዝቡን በማረጋጋት ላይ መሆኑን ጠቅሰው ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው እንዲመለሱና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም