የሰቆጣ ከተማ ባጃጆች በቤንዚን እጥረት ሥራ ለማቆም ተገደናል አሉ

56
ሰቆጣ ህዳር 7/2011 በዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ ከተማ ባለ ሦስት እግር ባጃጆች በቤንዚን እጥረት ሳቢያ ሥራቸውን እንዳቆሙ አሽከርካሪዎች ገለጹ። ከአሽከርካሪዎቹ አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት በከተማዋ የቤንዚን እጥረት መፈጠሩ በአገልግሎት አሰጣጣቸውና በኑሮአቸው ላይ ተጽዕኖ ፈጥሮባቸዋል። አቶ ደሱ ጎይቶም የተባሉት አሽከርካሪ በከተማዋ ከጥቅምት 26/2011 ጀምሮ አቅርቦት ባለመኖሩ ሥራቸውን ማከናወን እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ''በየዕለቱ ትምህርት ቤት በክፍያ የማመላልሳቸው የኮንትራት ተማሪዎችን ከማስተጓጎል ባለፈ የማገኘውን የዕለት ገቢ ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል‘’ ብለዋል። የጉዳዩ አሳሳቢነት ታይቶ ለችግሩ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል የሚሉት አሽከርካሪው፣ ካልሰሩ የተሽከርካሪዋን ዕዳ ለመክፈል እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ ሌላው አሽከርካሪ አቶ ደስታው ሙላው በበኩላቸው በእጥረቱ  ምክንያት ከአንድ ሳምንት በላይ ሥራ ማቆማቸውን አስረድተዋል፡፡ ‘’ተቀጥሬ ከማገኘው የዕለት ገቢዬ እንደቆመና ራሴን ችዬ የቀን ፍጆታዬን ለመሸፈን ተቸግሬያለሁ‘’ ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ በከተማ የባጃጅ አገልግሎት ባለመኖሩ ለዕንግልት ተዳርገናል የሚሉት ደግሞ የመንግሥት ሠራተኛዋ ወይዘሮ መዓዛ ፀመሩ ናቸው፡፡ ባጃጆቹ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ታሪፍ ይከፈልበት የነበረውን አገልግሎት ወደ አምስት ብር በማሳደጋቸው ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸዉን ተናግረዋል፡፡ የነዳጅ ማደያ ባለቤት የሆኑት አቶ ሺፈራው ገዛኸኝ በበኩላቸው' 'ከአሁን ቀደም እንቀዳባቸው ከነበሩት የመቀሌና ቆቦ ማደያዎች የአቅርቦት እጥረት አለብን ስላሉ ማምጣት አልቻልንም'' ብለዋል፡፡ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች መንገዱ  አመቺ አይደለም ስለሚሉ በአቅርቦቱ  ላይ እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ የዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ የሸማቾች ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ጌጡ አበበ በበኩላቸው በዞኑ እጥረቱ የተከሰተው በአገር አቀፍ ደረጃ ባለው እጥረት ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ በከተማዋ ያሉት ታፍና የተባበሩት ማደያዎች በመምሪያው በሚጻፍላቸው ደብዳቤ ከመቀሌ ማደያ ጣቢያዎቻቸው ይቀዱ እንደነበር ያወሱት ቡድን መሪው፣ከቆቦና ወልዲያ ማደያዎች እንዲቀዱ ቢሞከርም፤ እጥረቱ በፈጠረው ችግር አቅርቦቱን ማሟላት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ ችግሩ እስኪፈታ ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲጠብቅ የጠየቁት አቶ ጌጡ፣ቤንዚን በሕገ ወጥ መንገድ በማቅረብ በተጋነነ ዋጋ ለመሸጥ የሚደረግ ሙከራ ካለ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል። ሰቆጣ በአማራ ክልል የምትገኝ ከ30ሺህ በላይ ነዋሪዎች ያሏት ከተማ ናት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም