ኮንፌዴሬሽኖቹ የኢንዱስትሪ ሰላም ማስፈን በሚያስችሉ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኮንፌዴሬሽኖቹ የኢንዱስትሪ ሰላም ማስፈን በሚያስችሉ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት ተስማሙ
99
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 ኮንፌዴሬሽኖቹ የሰራተኞችን መብትና ጥቅም በሚያስከብሩና የኢንዱስትሪ ሰላም ማስፈን በሚያስችሉ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት ተስማሙ። የኢትዮጵያ አሰሪዎችና ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽኖች በጋራ የሚሰሩበት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ የሁለቱ ተቋማት በጋራ ጥቅሞች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማት የሰራተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር እንደሚያግዝ ተናግረዋል። ስምምነቱ ሰራተኞች ተደራጅተው ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚያደርጉትን ጥረትም ያጠናክረዋል፤ የአሰሪዎችና ሰራተኞችን ግንኙነትም በጋራ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል። በቀጣይ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የኢንዱስትሪ ሰላም ለማስፈን ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚሰሩም ገልጸዋል። ስምምነቱ የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላም፣ ጤናማ ግንኙነት መፍጠር፣ የስራተኞች መብት ማስከበርና ምርትና ምርታማነትን እንደሚያሳድግ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን ናቸው። ሰራተኞች ስራቸውን በአግባቡ መስራት፣ አሰሪዎችም የሰራተኞችን መብት ማስከበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል። በስራ ቦታዎች መልካም አስተዳደር ማስፈን የሚያስችሉ ተግባራትን በጋራ ለማከናወን ስምምነት መደረሱንም አክለዋል። ሁለቱ ኮንፌዴሬሽኖች የደረሱበትን ስምምነት በመተግበር የኢንዱስትሪን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ መስራት እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ግብሩ ናቸው። ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ለማረጋገጥና ለአገሪቱ ዕድገት ሁለቱ አካላት በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።