የአክሱም ከተማ ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል እያሳየ ነው---ተገልጋዮች

91
አክሱም ህዳር 7/2011 የአክሱም ከተማ ማዘጋጃ ቤት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል እየታየበት መሆኑን አስተያየት የሰጡ ተገልጋዮች ገለጹ፡፡ ከተገልጋዮቹ መካከል በከተማዋ  የማዕበል ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጎይተኦም መብራህቱ ለኢዜአ  እንዳሉት ከዚህ በፊት በማዘጋጃ ቤቱ አገልግሎት ለማግኘት ውጣውረድ የበዛበት ነበር፡፡ "በአሁኑ ወቅት አሰራሩ ተሻሽሎ  ያለምንም ማጉላላት ጉዳያችንን ፈጽመን ወደ ቤታችን  እየሄድን ነው" ብለዋል፡፡ "አሁን ወደ ማዘጋጃ ቤቱ የመጣሁት በመሬት ጉዳይ ውልና ማስረጃ ለመፈጸም ነው" ያሉት አቶ ጎይተኦም ሰራተኞቹ የስራ ሰዓታቸውን ጠብቀው ወደ ቢሮ በመግባት ተገልጋዮችን በጊዜ እያስተናገዱ መሆኑን መታዘባቸውን ተናግረዋል። በመተዋወቅና በዘመድ ሲካሄድ የነበረው ተግልጋዮችን  የማስተናገድ አሰራር በወረፋ ሲስተናገዱ መመልከታቸውን ተገልጋዩ መስክረዋል። ግብር ለመክፈል ወደ ማዘጋጃ ቤቱ የመጡት በአክሱም የሓየሎም ቀበሌ ነዋሪ  ወይዘሮ ልዕልቲ ተክላይ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ወደ መስሪያ ቤቱ ሲመላለሱ በስራ ሰዓት ቢሮው በተደጋጋሚ ተዘግቶ ያገኙት እንደነበር ተናግረዋል። በማዘጋጃ ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይም ብዙ እንግልትና ውጣውረድ ሲገጥማቸው መቆየቱን አስታውሰዋል። በከተማው ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ በማዘጋጃ ቤቱ በተመደቡ አዲስ አመራሮች የአሰራር እና የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "በማዘጋጃ ቤቱ አገልግሎት ለማግኘት ብዙ ሰው ቢኖሩም ሰራተኞቹ ለተገልጋዩ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት በደንበኞች አያያዝ ላይ የተሻለ አገልግሎት ተመልክቻለሁ" ሲሉ  ወይዘሮ ልእልቲ ተናግረዋል። ጉዳያቸው በአጭር ጊዜ እንደተፈጸመላቸውና በአገልግሎቱ እርካታ ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ  በከተማው የሊዝ ውል ለመፈጸም ወደ ማዘጋጃ ቤቱ የመጡ የከተማው ነዋሪ መምህር ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር ናቸው። የአክሱም ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ክንፈ እንደገለጹት የከተማው ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በተደረገው የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ የተገኙ ክፍተቶችን ለመሙላት እየተሰራ ነው። "ከተለያዩ ከተሞች ተሞክሮ  ወስደናል፣ በአገልገሎት አሰጣጥና አሰራር ላይ ያሉብንን ክፍተቶች ለመሙላት ህዝቡ እያበረታታን ነው" ያሉት ስራ አስኪያጁ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተጀመረውን የለውጥ ስራ ለማስቀጠል በትጋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ የማዘጋጃ ቤቱን አዲስ  አሰራር ከመዘርጋት ባለፈ ሰራተኛው የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጣ መደረጉን ገልጸው በስብሰባ ምክንያት ይደርስ የነበረው የተገልጋዮች እንግልትና መጉላላት መቅረቱን ገልጸዋል። እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ የስራ ሰዓት በማያከብሩ ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል፤ የተጠያቂነትና የግልጽነት አሰራር እንዲጠናከር እየተሰራ ነው፡፡                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም