በሶማሌና ጋምቤላ ክልሎች የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ ተከሰተ - የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት

56
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 በሶማሌና ጋምቤላ ክልሎች የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ መከሰቱን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ገለፀ። በክልሎቹ በሽታው በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ ሪፖርት ከተደረገበት ዕለት ጀምሮ በሽታውን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት፣ የበሽታዎች ቅኝትና ምላሽ የመስጠት ተግባራት እያከናወንኩ ነው ብሏል። የበሽታው ቅኝትና ክትትል ሥራ በሌሎችም ክልሎች በተጠናከረ መልኩ እያከናወነ መሆኑንም አስታውቋል። ወረረሽኙ በሶማሌ ክልል በዳዋ ዞን በሁደት፣ ቀደዱማ፣ ሙባራክና ሞያሌ ወረዳዎች፣ በሊበን ዞን በዴካ ሱፍቱና በቁሎማዮ ወረዳዎች እንዲሁም በፋፈን ዞን ባቢሌ ወረዳ የተከሰተ ሲሆን በጋምቤላ ክልል ደግሞ በጋምቤላ ከተማ ዙሪያ በአቦቦ ወረዳዎች ተከስቷል። በሽታው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በማሳልና በማስነጠስ ወቅት ከአፍና አፍንጫ በሚወጣ እርጥበት አማካኝነት ሲሆን በክልሎች በሽታው እንዲሠራጭ ያደረጉት አጋላጭ ሁኔታዎች መካከል ያልተከተቡ ህፃናት መኖራቸው ነው ብሏል። በኢንስቲትዩት የሚመራ በአገር ዓቀፍና በክልል ደረጃ ከጤና ጥበቃ፣ ከዓለም ጤና ድርጅት፣ ከዓለም ዓቀፉ የሕፃናት አድን ድርጅትና ከድንበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን የተውጣጡ የሕብረተሰብ አደጋ ቁጥጥር፣ የበሽታዎች ቅኝት፣ የሐኪሞችና የክትባት ባለሙያዎች ያሉበት  ቡድን ተቋቁሞ ምላሽ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል። በሶማሌ ክልል ከ300 ሺህ በላይ ለሚሆኑና ከስድስት ወር እስከ 15 ዓመት ዕድሜ ክልል ለሚገኙ ህፃናት ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ወረዳዎች ክትባቱ በዘመቻ መልክ እየተሰጠ እንደሚገኝም የኢንስቲትዩቱ መግለጫ አትቷል። በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልል 352 ሺህ ለሚሆኑ ከ6 ወር እስከ 15 ዓመት ዕድሜ ክልል ለሚገኙ ህፃናት ክትባቱን በሁሉም ወረዳዎች በዘመቻ መልክ ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም