በምዕራብ ጎጃም የደን ሽፋኑን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

58
ባህርዳር ህዳር 7/2011 በምዕራብ ጎጃም በክረምት ወቅት የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የደን ሽፋኑን 19 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ። በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ቡድን መሪ አቶ ምንውየለት ገበየሁ  ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፈው የክረምት ወቅትም በ22 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ 135 ሚሊዮን ችግኞች በመትከል ማህበረሰቡ ጥበቃና እንክብካቤ እያደረገ  ነው፡፡ ቀደም ሲል ማህበረሰቡ ችግኝ የሚተክለው በራሱ ተነሳሽነት ሳይሆን በጉትጎታ እንደነበር አስታውሰው  ደን የሚያስገኘውን ጥቅም  እየተረዳ በመምጣቱ የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ የማሳደግ ልምዱ እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል። እንደ ቡድን መሪው ገለጻ በየዓመቱም የተራቆቱ ቦታዎችን በባለቤትነት መንፈስ በደን መልሶ የመሸፈን ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ በክረምቱ ከተተከሉት መካከል ባህርዛፍ፣ ኮሶ፣ ፅድ፣ ዝግባና ሌሎች ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የዛፍ ችግኞች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል። በግልና በወል መሬቶች የሚተከሉ ችግኞችንም ህብረተሰቡ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በመጠበቅ እየተንከባከበ ነው። ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የችግኝ ተከላና የደን እንክብካቤ ስራ የደን ሽፋኑን 17 በመቶ ማድረስ መቻሉን ያስረዱት አቶ ምንውየለት በተያዘው ዓመትም የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ በማጽደቅ 19 በመቶ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል። በጃቢጠህናን ወረዳ የሰጎዲት መቅረጫ ቀበሌ አርሶ አደር ሞላ ውድነህ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በክረምት ወቅት ችግኝ የሚተክሉት በራሳቸው ተነሳሽነት ሳይሆን በጉትጎታ እንደነበር አስታውሰዋል። አርሶ አደሩ እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደን ስለሚያስገኘው ጠቀሜታ በባለሙያዎች ግንዛቤ እያገኙ በመምጣታቸው በግልና በወል መሬት የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክበው በማሳደግ አካባቢው መልሶ በደን እንዲለብስ እየተደረገ ነው። "የደንን ጠቀሜታ ከራሴ ህይወት ለይቼ ስለማላየው  የሚተከሉ ችግኞችን በተለየ ትኩረት እንከባከባለሁ" ያሉት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር አለኽኝ ስመኝ ናቸው። የቡሬ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አያና ቢተው በበኩላቸው የተራቆቱ መሬቶችን በደን መልሶ የማልበስ ስራ ከጀመሩ ከአምስት ዓመታት  በላይ እንደሆናቸው ተናግረዋል። ባለፈው የክረምት ወቅትም በወል ከተከሉት በተጨማሪ በግላቸው ከ2 ሺህ በላይ ችግኞችን ተክለው እየተንከባከቡ መሆናቸውን አስረድተዋል። በ2009 ዓ.ም. የክረምት ወቅት ከተተከለው ከ118  ሚሊዮን በላይ ችግኝ  81 በመቶው መጽደቁን  ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም