ፍርድ ቤቱ በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት ኮሎኔል አሰፋ ዮሃንስ ለህዳር 11 እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጠ

62
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት ኮሎኔል አሰፋ ዮሃንስ ጠበቃ ለማቆም አቅም የለኝም በማለታቸው ለህዳር 11 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርቡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ። የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ሃላፊ በነበሩበት ወቅት ያለአግባብ የአገር ሃብት እንዲባክንና ለሁለት የውጭ አገር ድርጅቶች ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ የሙስና ወንጀል ጠርጥሮ ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ለፍርድ ቤት አስረድቷል። አንዱ ድርጅት ያለጨረታ ስራውን እንዲወስድና በ49 ሚሊዮን ዶላር እንዲከናወን የተዋዋለውን ውል ወደ 55 ሚሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል በማድረግ ወንጀል ጠርጥሯቸዋል። ሌላኛውም ድርጅት በተመሳሳይ ያለጨረታ የስድስት ሚሊዮን ዶላር ስራ እንዲወስድና ስራውን ሳያከናውን ክፍያ እንዲፈጸምና ስራውን ሳይጨርስ እንዲሄድ በመፍቀድ የአገር ሃብት እንዲሸሽ አደርገዋል ብሏል። ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብም ፖሊስ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል። ቢሆንም ግን ተጠርጣሪው ጠበቃ በራሳቸው ለማቆም የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው በመግለጽ መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠይቀዋል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ህዳር 11 ቀን ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቷል። በተያያዘም ፖሊስ በሙስና ወንጀል የጠረጠራቸውን ኮሎኔል ጉደታ አለነ፣ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ እና ኮሎኔል ሰጠኝ ካሳዬን ፖሊስ ፍርድ ቤት አቅርቦ የነበረ ቢሆንም አቤቱታው ተስተካክሎ እንዲቀርብ በማለት ፍርድ ቤቱ ለሰኞ ህዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል። አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም የመስቀል አደባባይ ጥቃት እጃቸው አለበት በሚል ተጠርጥረው የተያዙና በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም