ታላቁ ሩጫ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ለሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ተለዋጭ መንገዶች ተዘጋጅተዋል

108
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 በመጪው እሁድ የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በሚያካልላቸው አካባቢዎች የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙባቸው ተለዋጭ መንገዶች ይፋ ሆነዋል። 44 ሺህ ሯጮችን የሚያሳትፈው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከነገ በስትያ መነሻና መድረሻውን ስድስት ኪሎ የሰማዕታት ሐውልት አድርጎ ይከናወናል። ሩጫው ከስድስት ኪሎ አደባባይ ተነስቶ ምኒሊክ ሆስፒታል-ቀበና-እንግሊዝ ኤምባሲ-በሾላ ገበያ ዞሮ በሱመያ መስጊድ-ሲግናል-አቧሬ-ራስ አምባ ሆቴል አድርጎ ወደ አራት ኪሎ በመሄድ ፍጻሜውን ስድስት ኪሎ አደባባይ ያደርጋል። ይህን ተከትሎም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በዚህ አካባቢ የሚያልፉ አሽከርካሪዎች የሚጠቀሟቸውን ተለዋጭ መንገዶች ይፋ አድርጓል። በዚህ መሰረት ከጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ወደ ሽሮ ሜዳ ፈረንሳይ ለጋሲዮን የሚሄዱ አሽከርካሪዎች ከጊዮርጊስ- በአፍንጮ በር-በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአልአቅሳ መስጊድ ወደ መነን አቅጣጫ መጠቀም ይችላሉ። ከሽሮ ሜዳና ፈርንሳይ መስመር ተነስተው ወደ ስድስት ኪሎ፣ አራት ኪሎና መስቀል አደባባይ የሚጓዙ ደግሞ በተለዋጭነት በአፍንጮ በር- ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን-ቸርችል ጎዳናን ይጠቀማሉ። እንዲሁም ከሽሮ ሜዳ ተነስተው ወደ መገናኛና ቦሌ አቅጣጫ የሚሄዱ አሽከርካሪዎች በአፍንጮ በር-ጊዮርጊስ አድርገው በቸርችል ጎዳና ኢሚግሬሽን-በካሳንቺስ-ኡራኤል ቤተክርስቲያን አድርገው ወደ መገናኛ መጓዝ ይችላሉ ብሏል። በተጨማሪም ከነገ ህዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም ጠዋት ጀምሮ ሩጫው በሚካሄድባቸው መንገዶች ላይ አሸከርካሪ አቁሞ መሄድ የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።                              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም