ደብረ ብርሃን ከአዲስ አበባ የሚያገናኛት ደረጃውን የጠበቀ የፍጥነት መንገድ ትሻለች

184
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 ደብረ ብርሃን በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ የተሻለ እንቅስቃሴ ብትጀምርም ከአዲስ አበባ የሚያገናኛት ፈጣን መንገድ አለመኖሩ በተጠቃሚነቷ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ። ከተማዋን ከአዲስ አበባ የሚያገናኝ ደረጃውን የጠበቀ የፍጥነት መንገድ እንዲገነባም ጠይቋል። አፄ ዘርዓ ያቆብ የቆርቆሯትና ለ14 ዓመታትም የነገሱባት   ጥንታዊቷ ደብረ ኢባ የዛሬዋ ደብረ ብርሃን የተመሰረተችው በ1446 ዓ.ም እንደሆነ ይነገራል። ይሁንና የዕድሜዋን ያህል እድገት ያላሳየችና የቆረቆዘች ከተማ ሆና መቆየቷ ይነሳል። "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት በኢንቨስትመንት መነቃቃት ጀምራለች" ያሉት የከተማዋ ቤቶችና ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ሰለሞን ጌታቸው ለአዲስ አበባ ካላት ቅርበት አኳያ "የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ የመሆን ዕድል አላት" ይላሉ። "በከተማዋ ሆቴሎች መገንባት ጀምረዋል" የሚሉት አቶ ሰለሞን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ እንድትሆን ለማድረግም በአማራ ክልል ፈቃድ ከተሰጣቸው ባለ ኮከብ ሆቴሎች መካከል አምስቱ በደብረ ብርሃን እንዲገነቡ መወሰኑን ገልጸዋል። ከተማዋ የኢንዱስትሪ ማዕከልም እየሆነች በመምጣቷ የመንገድ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል። በቂ የተፈጥሮ ሃብት፣ ምቹ የአየር ንብረት ያላትና ሰላማዊ ከተማ መሆኗን ገልጸው በተለያዩ የልማት መስኮች መሳተፍ ለሚሹ አካላት ከተማ አስተዳደሩ እገዛ በማድረግ ላይ እንደሆነ አንስተዋል።  ነገር ግን የአገሪቱ መዲና፣ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ከተማ ከሆነችው አዲስ አበባ በ130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ደብረ ብርሃን ደረጃውን በጠበቀ የመንገድ መሰረተ ልማት 'መገናኘት አልቻለችም' ብለዋል። ይህም ከተማዋ በተለይም በኮንፈረንስ ቱሪዝም መስክ ተጠቃሚ እንዳትሆን የራሱ አሉታዊ ተዕጽኖ እንዳለው ጠቁመዋል።  የደብረ ብርሃን-አዲስ አበባ መንገድ በትራፊክ አደጋ ከፍተኛውን ድርሻ እየያዘ የመጣ መስመር እንደሆነና ከአዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን ከሌሎች የዞኑ ከተሞች ጋር የሚያገናኛት ደረጃውን የጠበቀ መንገድ እንደሌላትም አንስተዋል። በሌላ በኩል የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ ፈጣን የባቡር መስመር ከተማዋን ሳይነካ መገንባቱ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ "ቅሬታ ፈጥሯል" ነው ያሉት። የፈጣን ባቡር መስመር ባታገኝም ከአዲስ አበባ የሚያገናኛትና እንደ ሌሎች የመዲናዋ ቅርብ ከተሞች በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ የሚያደርጋት የፍጥነት መንገድ ሊገነባላት እንደሚገባ አመልክተዋል።  በሌላ በኩል በከተማዋ ይገነባል የተባለውና እስካሁን ያልተጀመረው የደረቅ ወደብ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠውና ከተማዋን የሚያገናኙ መስመሮች ደረጃም እንዲሻሻል ጠይቀዋል።                              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም