ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከትግራይ ምዕራባዊ ዞን የህዝብ ተወካዮች ጋር ተወያዩ

60
መቀሌ ህዳር 7/2011 የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በወቅታዊ ጉዳይና በልማት ዙሪያ ከምዕራባዊ ዞን የህዝብ ተወካዮችና ባለሀብቶች ጋር ተወያዩ፡፡ በውይይቱ ወቅት ለተነሱ ጥያቄዎች  ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ በውይይቱ ወቅት ከሙስና ጋር በተያያዘ  ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ "ክልሉ የተጠርጣሪ መደበቅያ አይሆንም በህግ የሚፈለግ ተጠርጣሪ ካለ አሁንም የክልሉ መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን ይሰራል "ብለዋል፡፡ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ሆነ ህዝብ የታገሉት የህግ በላይነት ለማረጋገጥ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የህዝብን ሀብት የዘረፈ በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ ተጠርጣሪ ካለ ለህግ መቅረብ  እንደሚገባ  አመልክተዋል፡፡ " የክልሉ ህዝብ እንደወትሮው አንድነቱ አጠናክሮ ለሰላም ያለው ፅኑ እምነት በተግባር ማሳየቱ ሊመሰገን እና አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የጸገዴ ወረዳ ነዋሪ አባ መንግስቴ አለሙ  የወረዳው ህዝብ የማይወክልዋቸው ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች በመሆን አዲስ ማንነት ለማልበስ  የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መንግስት ስርዓት ማሲያዝ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ የወልቃይት ወረዳ ነዋሪ አቶ ማማይ ጎበየ  በበኩላቸው ህዝብና መንግስት ለመረበሽና ልማት ለማደናቀፍ የሚሰሩ  ሰዎች መንግስት እንዲታረሙ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በቃፍታ ሁመራ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ አማኑኤል ተስፋዬ  የእርሻ ኢንቨስትመንቱ ለማዘመን መንግስት ምን እየሰራ እንደሆነ ላቀረቡት ጥያቄ የምዕራባዊ ዞን የልማት ኮሪደር በመሆኑ  አደረጃጀቱ ሆነ የሃብቱ አጠቃቀም በምሁራን በመጠናት ላይ እንዳለ ዶክተር  ደብረጽዮን በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል፡፡ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ፈጣን ለውጥ የሚያመጣ አሰራርና አደረጃጀት እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡ ቀበሌ ከቀበሌ የሚያገናኝ መንገድ እንዲሰራላቸው ላቀረቡት ጥያቄም  በፀገዴ ወረዳ ስድስት ቀበሌ ገበሬ ማህበራት የሚያገናኝ  የጠጠር መንገድ  በበጀት ዓመቱ  እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች ከማንነት፣ ከጤና፣ ከመጠጥ ውሃና ከመንገድ ግንባታ ጋር በተያያዘ  ላነሷቸው ጥያቄዎች ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩና  ሌሎች የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ትናንት በተካሄደው በዚሁ ውይይት ከዞኑ አራት ወረዳዎች የተውጣጡ የህዝብ ተወካዮችና ባለሀብቶች ተሳትፈዋል፤ ዶክተር  ደብረጽዮን ዛሬ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች ጉብኝት እያደረጉ ነው፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም