የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሄደ

106
አዲስ አበባ  ግንቦት 15/2010  የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት ጫወታዎች ዛሬ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሂደዋል። አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በተደረገ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአሜ መሐመድ ብቸኛ ጎል ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት አሸንፏል። በክልል ከተሞች አዳማ ላይ መቐለ ከተማ አዳማ ከተማን ሁለት ለዜሮ፣ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ መከላከያን አንድ ለዜሮ፣ ሃዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ፋሲል ከተማን ሁለት ለዜሮ እንዲሁም ሰበታ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ወልዲያ ከተማን ሶስት ለዜሮ በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ ሁለት ለአቻ የተጠናቀቀ ሲሆን ጅማ ላይ በተደረገ ጨዋታ መሪው ጅማ አባ ጅፋር ከአርባ ምንጭ ከተማ ያለ ምንም ግብ ተለያይተዋል። ከቀኑ አስራ አንድ ሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም ቀሪ አንድ ጨዋታ በደደቢትና በኢትዮ ኤሌትሪክ መካከል የተደረገ ሲሆን ኢትዮ ኤሌትሪክ ደደቢት አራት ለሶስት አሸንፏል። በዚሁ መሰረት የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ጅማ አባጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 40 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው እንደቅደም ተከተላቸው አንደኛና ሁለተኛ ሲሆኑ፤ መቐለ ከተማ  በ39 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባጅፋሩ ናይጄሪያዊው ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ በ14 ጎሎች ሲመራ፤ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና የአዳማ ከተማው ዳዋ ሁቴሳ በተመሳሳይ ዘጠኝ ግቦች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም