በአማራና ደቡብ ከአንድ ሚሊዮን 400ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመስኖ ሊለማ ነው

51
አዳማ ህዳር 7/2011 በአማራና ደቡብ ክልሎች በተያዘው  ዓመት ከአንድ ሚሊዮን 400ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት  በመስኖ ለማልማት እየተሰራ መሆኑ  ተገለጸ፡፡ በባህላዊና ዘመናዊ መስኖ በሁለት ዙር  ከሚለማው ከዚሁ መሬት ውስጥ ከ945 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአማራ ክልል ውስጥ ነው፡፡ በክልሉ ግብርና ቢሮ የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ድልነሳው ለኢዜአ እንዳሉት ምርትና ምርትማነትን ለማሳደግ ከሚለማው መሬት 96 በመቶ በመስመር ለመዝራት ታቅዶ እየተሰራ ነው። ከ2 ሚሊየን አርሶ አደሮች በላይ  በማሳተፍ ተጠቃሚ ለማድረግ በዕቅድ ተይዞ ተግራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቷል። እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴም  ታርሶና ለስልሶ ከተዘጋጀው 34 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ውስጥ 19 ሺህ 588 ሄክታሩ ገበያ ተኮር በሆኑ የአዝርዕት፣ ስራስር፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘሮች መሸፈኑን ዳይሬክተሩ  ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የዘንድሮውን የመስኖ ልማት ለማስፈጸም ከ587 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እየተሰራጨ ነው። ከልማቱም 144 ሚሊዮን 329 ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል። በተመሳሳይ የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለፁት በክልሉ በበጀት  ዓመቱ ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ። ለልማቱ  የሚውሉ የተለያዩ የውሃ አማራጮች መመረጣቸውን ያመለከቱት ኃላፊው አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማቅረብ  ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት እስካሁንም  314 ሺህ 390 ሄክታር መሬት በማረስ የማሳ ዝግጅት ተደርጓል፤ ከዚህም  36 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ  በአትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬና በአገዳ ሰብል ተሸፍኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም