የህዝብና የመንግስት ሃብት ዘርፎ ማምለጥ አይቻልም---የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች

74
መቀሌ ህዳር 6/2011 የሀገር ሃብት በመዘረፍና በሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ሰዎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና ባለሞያዎች ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ የህዝብና የሃገር ሃብት የዘረፉ አካላት እና ተቋማት ሁሉ ተገቢውን ፍርድ ሊያገኙ እንደሚገባ ጠቁመዋል። አቶ ገብረኪዳን ሀዱሽ የተባሉ የመቐለ ነዋሪ እንደገለጹት መንግስት ሰሞኑን እየወሰደ ያለውን እርምጃ ጊዜ  ይወስዳል እንጂ የህዝብና የመንግስት ሃብት ዘርፎና ሰብአዊ መብት ጥሶ ማምለጥ እንደማይቻል የሚያስተምር ነው። በዚህ አጋጣሚ ግን አንዱ የሚጠየቅበት ሌላው የሚተውበት ሁኔታ እንዳይፈጠር መንግስት ጥንቃቄ ማድረግ  እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ የታገለውና መስዋእትነት የከፈለው የህግ ልእልና እንዲረጋገጥና ሁሉም በህግ እንዲገዛ መሆኑን አቶ ገብረኪዳን ገልጸዋል፡፡ የህግ ልእልና የማስከበር ጉዳይ ለማንም ሰው እንደስጋት መታየት የለበትም ያሉት አቶ ገብረኪዳን የእርምጃ አወሳሰዱ ትክክለኛነት ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ሌላው የከተማው ነዋሪ  ወይዘሮ ገነት ግርማይ እንዳሉት የትግራይ ህዝብ የታገለው ሰብአዊ ክብሩንና መብቱን ለማስከበር ነው። "ትግላችን ሀብት ሲዘረፍ አይተን እንደላየን ማለፍ ሳይሆን ፈጻሚዎቹን ማጋለጥ ነው" ያሉት ወይዘሮዋ የትግራይ ህዝብ ለጥፋተኛ ምሽግ ሳይሆን መንጥሮ የሚያወጣ ህዝብ መሆኑን ገልፀዋል። "በሀብት ዘረፋ ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር የዋሉ ሰዎች ዘረፋውን የፈጸሙት አለቃና ሰራተኛ ባለበት የመንግስት ተቋም በመሆኑ በየደረጃው ሁሉም መጠየቅ አለበት" ብለዋል፡፡ "ወንጀል ፈጻሚው በጥፋቱ ሊቀጣ ይገባል" ያሉት ወይዘሮ ገነት በወንጀሉ የተሳተፉት አካላት በሙሉ ተገቢው ጥንቃቄ ተደርጎ ፍትህ ሊሰጥባቸው እንደሚገባ አስረድተዋል። "የሀገር ሀብትና የዜጎች መብት ሲጣስ አንዱ ከሌላው ሳይለይ ሁሉም በጋራ ነው መታገል ያለበት" ብለዋል፡፡ መንግስት በየደረጃው የነበረውን ያጠፋ ሃላፊ በጥፋቱ መጠን መጠየቅ አለበት ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አስቴር ተዓረ ናቸው፡፡ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ግጭትን ከሚቀሰቅስ ስሜታዊ ከሆነ ዘገባ መቆጠብ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም