በማህጸን ጫፍ ካንሰር ላይ የሚሰሩ ጥናቶችን ድግግሞሽ ሊያስቀር የሚያስችል ቡድን ተዋቀረ

126
አዲስ አበባ ህዳር 6/2011 በማህጸን ጫፍ ካንሰር ላይ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች እንዳይደጋገሙ የሚደግፍ  ቡድን መዋቀሩን የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት አስታወቀ። ኢኒስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴርና በዘርፉ ከሚሰሩ ምሁራን ጋር በማህጸን ጫፍ ካንሰር ዙሪያ በተሰሩ ጥናትና ምርምሮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ በማህጸን ጫፍ ካንሰር ላይ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች ተደጋጋሚ በመሆናቸው ችግር ፈቺ የህክምና ውጤት ይዞ በመምጣት ረገድ ክፍተቶች አሉ። በተጨማሪም ምርምርና ጥናቶቹ ውጤት የማያስገኙና ከፍተኛ የኃብት ብክነት የሚያስከትሉ እንደነበር ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል። ቀደም ሲል ኢኒስቲትዩቱን ጨምሮ አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ መቀሌ፣ አክሱም፣ ጎንደር ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩትና አርማወር ሃንስ የምርምር ኢንስቲትዩት በማህጸን ጫፍ ካንሰር ላይ ያተኮሩ ጥናትና ምርምሮችን አካሂደዋል። ይሁን እንጂ ጥናቶቹና ምርምሮቹ በተለያዩ አካላት በመሰራታቸው ተጨባጭ መረጃ በመስጠት በኩል ውጤታማ መሆን አልተቻለም። ክፍተቱን ለመሙላት ከተቋማቱ በተውጣጡ ሙያተኞች ራሱን የቻለ ቡድን በማዋቀር በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ ግኝቶችን ማስረጽ አስፈላጊ በመሆኑ ቡድኑ ወጥነት ያለው ስራ በመስራት የተሻለ የምርምር ውጤት ማበርከት ይጠበቅበታል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ። በተጨማሪም በተቋም ደረጃ የተሰሩ ምርምሮችን ወደ አንድ ማምጣት፣ ማሻሻያዎችን በማከል፣ የመረጃና የእውቀት ልውውጥ በማድረግ የምርምር ውጤቶች እንዳይደጋገሙ በሚያስችል መልኩ በጋራ በመስራት አመርቂ ውጤት ለማምጣት ቡድኑ የጎላ ሚና እንደሚኖረው አክለዋል። በቀጣይም በምርምሩ የሚገኙ ግኝቶችን መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ደረጃ በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ላይ ብቻ የሚሰራ ተቋም ለማቋቋም መታቀዱን ተከትሎ ቡድኑ የሚያመጣው ውጤት ለእቅዱ በግብአትነት እንደሚያገለግል አስረድተዋል። የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የጨመረውን የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ መንስኤ መለየትና መከላከል ላይ አመርቂ ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ተናግረዋል። በሚኒስቴሩ የካንሰር መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ ዶክተር ኩኑዝ አብደላ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ ለመከላከልና ለመግታት በግብአትነት የሚጠቀማቸው የጥናትና ምርምር ውጤቶች በሚፈለገው ደረጃ እገዛ እያደረጉ አይደለም። ችግሩን ለመቅረፍና ወጥነት ያለው ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ለማበርከት ሙያተኞች በጋራ መስራታቸው እንደ ዋነኛ አማራጭ መወሰዱ ተገቢ እንደሆነ አመላክተዋል። በተለይም ሚኒስቴሩ በቅርቡ ለሚጀምረው የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ውጤታማ እንዲሆን ቡድኑ ተገቢውን መረጃ በማሰባሰብ የሚያከናውነው ጥናት ክትባቱን ተግባራዊ ለማድረግ እገዛ ያደርጋል። በተጨማሪም በጉዳዩ ዙሪያ አገር በቀል መረጃ እንዲኖር ያስችላልም ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የማህጸን ጫፍ ካንሰር በሽታ ሁለተኛው ገዳይ የካንሰር በሽታ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም