በኦሮሚያ ክልል ከ700 ሺህ ቶን በላይ ቡና ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

66
ጅማ/አዳማ  ህዳር 6/2011 በኦሮሚያ ክልል ከ700 ሺህ ቶን በላይ ቡና ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ። በጅማ ዞን 52 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የክልሉ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ዳባ ጅንፌሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ከ700 ሺህ ቶን በላይ ቡና ምርት ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡ በተያዘው የበጀት አመት ከአምናው የተሻለ ምርት ለማግኘት አምራቹ አርሶ አደር የተሟላ የቡና ኤክስቴሽን አገልግሎትና ሙያዊ ድጋፍ በመሰጠቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ የምርት ጭማሪ እንደሚኖር አመልክተዋል። የቡና ምርት ጥራትን ለመጠበቅ በምርቱ አሰባሰብ፣ አያያዝ፣ ማከማቸትና መላክ ላይ  አርሶ አደሮች ባለሙያዎች በቂ ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል። በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የኤክስቴሽን ስርፀት ባለሙያ አቶ ሚሬሳ ፊጤ በበኩላቸው በክልሉ የቡና  ምርታማነትን ለመጨመር የተሻሻሉ የቡና  ዝርያዎችን የማባዛትና ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። በግብርና ምርምር ማዕከላት የተዘጋጁ ከ1 ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኞች በሁሉም የክልሉ ዞኖች ለሚገኙ አርሶ አደሮች መሰራጨታቸውን ባለሙያው አስረድተዋል። በተመሳሳይ መልኩ በጅማ ዞን 52 ሺህ ቶን የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ቡናና ሻይ ባለስልጣን መስሪያ ቤት አስታውቋል ። የባለስልጣኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ረጋሳ እንደገለጹት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ከታቀደው 52 ሺህ ቶን ቡና ውስጥ 31 ሺህ 540 ቶን የታጠበ መሆኑን ተናግረዋል ። የጅማ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ኡመታ በጅማ ዞን ውስጥ ከሚገኘው 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ 65 በመቶ የሚሆነው ኑሮው በቡና ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አምራቹ ከምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ  520 አንደኛ ደረጃ የቡና መገበያያ ጣቢያዎች   በቅርበት ሆነው የግብይት ስራው በማሳለጥ ላይ እንደሚገኙ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ባለፈው የበጀት አመት ከተሰበሰበው ከ500 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት 214 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ከክልሉ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም