በትግራይ ምእራባዊ ዞን የወባና ካልአዛር በሽታ እየቀነሰ ነው ተባለ

71
ሁመራ ህዳር 6/2011 በትግራይ ምእራባዊ ዞን ቆላማ በሽታዎችን ለመከላከል በተሰጠ ትኩረት የወባና ካልአዛር በሽታ እየቀነሰ መምጣቱን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የዘርፍ አስተባባሪ አቶ ደብረብርሃን ብርሃነ ለኢዜአ እንደገለጹት የዞኑ ህብረተሰብ የጤና ችግር የሆኑትን  የወባና የካልአዛር በሽታዎች ለመከላከል በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከተከናወኑ ተግባራት መካከልም ስለ በሽታዎች ምንነት፣ መተላለፍያና መከላከያ መንገዶች ለህብረተሰቡ ሰፊ ትምህርት መስጠት ይገኝበታል፡፡ እንዲሁም ህብረተሰቡ በተለይ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ረግረጋማ አካባቢዎችን በማፋሰስ፣ በማዳፈንና በማጨድ በወባ መከላከልና ቁጥጥር ስራው በስፋት እንዲሳተፍ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በዞኑ አራት ወረዳዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች 101 ሺህ 524 የወባ መከላከያ አጎበር መሰራጨቱን አስታውቀዋል፡፡ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶም ሰራተኞቻቸው ከወባና ካልአዛር በሽታ እንዲጠበቁ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲጫወቱ የሚያስችል ቅንጅት መፈጠሩን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ በዚህም  በወባና ካልአዛር በሽታዎች የሚያዙ ነዋሪዎች ቁጥር በየአመቱ እየቀነ የመጣ ሲሆን በተለይ በወባ በሽታ የሞተ ሰው አለመኖሩን አስታውቀዋል፡፡ የካላዛር በሽታም በ2008 ዓም 277 የነበረው የህሙማን ቁጥር ባለፈው አመት ወደ 30 ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የወባም ሆነ የካላዛር በሽታዎች ለመከላከል  ከጤና ባለሞያዎች ጋር በቅንጅት እንሰራለን ያሉት ደግሞ በቃፍታ ሑመራ  ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ አቶ ተክኤ ባህታ ናቸው፡፡ ባለሀብቱ እንዳሉት ባለፈው አመት በአረምና በአጫዳ ወቅት በበሽታው የተያዙ ሰራተኞች ለማሳከል እስከ 200 ሺህ ብር ወጪ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ሌላው በእርሻ ኢንቨርስትመን የተሰማሩት አቶ ተሻለ አብርሃ  በበኩላቸው  መንግስት ለጤና በሰጠው ልዩ ትኩረት  ባለሙያዎችን በመላክ ሰራተኞቻቸው እንደሚከታተሉላቸው ገልጸዋል፡፡ ለወባ መድሃኒትና ለአጎበር መግዣ በጀት በመመደብ የቆላማ በሽታዎች ለመከላከል ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  በቃፍታ ሁመራ ወረዳ በእርሻ ስራ የተሰማሩ አቶ መሓመድ ዓንደይ ናቸው፡፡ በዚህ አመት በአረምና በአጭድ ወቅት ሁለት ጊዜ በወባ መታመሙን የተናገረውና በቀን ስራ የሚተዳደረው ወጣት የእብዮ መስፍን በበኩሉ በፍጥነት የወባ መድሃኒት በማግኘቱ የቀን ስራውን ሳይሰተጓጉል ወደ ስራ መመለሱን ተናግሯል፡፡ በካልአዛር በሽታ ተይዞ በካህሳይ አበራ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተል ኢዜአ የነጋገርው ወጣት ተክለወይኒ ገብረ መድህን በበኩሉ በህክምና ባለሙያዎች ክትትል እየተደረገለት መሆኑን ገልጿል፡፡ ሆስፒታሉ ህክምና መከታተል ከጀመረ አንድ ሳምንት ማስቆጠሩንን የተናገረው ወጣቱ በተደረገለት ክትትል ጤንነቱ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡ የካልአዛር በሽታ ሳንድ ፍላይ ተብላ በምትጠራ ተባይ የሚመጣና ገዳይ ከሆኑ የቆላ  በሽታዎች አንዱ መሆኑን ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም