በአምራቹና በሸማቹ መሀከል ያለው የላላ የገበያ መረጃ አቅርቦት ከምርቱ ዋነኛው ተጠቃሚ ደላላው እንዲሆን እንዳደረገው ተገለጸ

86
አዳማ ህዳር 6/2011 በአምራቹና በሸማቹ መሀከል ያለው የላላ የገበያ መረጃ አቅርቦት  ከምርቱ ዋነኛው  ተጠቃሚ ደላላው እንዲሆን እንዳደረገው ተገለጸ፡፡ ዘመናዊ የገበያ መረጃ ስርዓት ለመዘርጋት መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑንም የፌዴራል ህብረት ስራ  ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡ በሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ የገበያ ተደራሽነት አስተባባሪ አቶ በሬቻ ጡሪ ለኢዜአ  እንደገለጹት አንድ ምርት ከአርሶ አደሩ እጅ ወጥቶ አዲስ አበባ ሸማቹ እጅ እስኪገባ ድረስ ከ6 እስከ 10 የሚደርሱ ደላሎች እጃቸውን ያስገባሉ ። ባቱ ከተማ አካባቢ በስፋት የሚመረቱት ቲማቲምና ሽንኩርት የመሳሰሉ አትክልቶች ከአርሶ አደሩ ማሳ በአምስት ብር ሂሳብ ገዝተው እዛው አንድ ኪሎ ሜትር በማይሞላ ርቀት ውስጥ አስፋልት ዳር ላይ ኪሎውን በ9 ብር ሒሳብ የሚሸጥበት አጋጣሚ መኖሩን አስተባባሪው ተናግረዋል። ምርቱ ሸማቹ እጅ እስኪገባ ድረስ ዋጋው በእጥፍ የሚጨምርበት አጋጣሚ ቢኖርም ዋናው ተዋናይና ተጠቃሚ የሚሆነው የገበያ ዋጋን እስከ መወሰን ጭምር የሚደርሰው ደላላው መሆኑን አቶ በሬቻ አስረድተዋል ። ደላላ አስፈላጊ አይደለም የሚል ሃሳብ የለኝም ያሉት አስተባባሪው የተንዛዛና የግብይት ሂደቱን እስከማወሳሰብ የሚደርሰ ግን መሆን የለበትም ብለዋል ። በፌዴራል ህብረት ስራ  ኤጀንሲ የህብረት ስራ ግብይት ዳይሬክቶሬት የህብረት ስራ መረጃ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዳሳ ዳና በበኩላቸው የደላሎች  ጣልቃ መግባት የምርት ግብይት ሂደቱን እያዛባው እንደሚገኝ ይስማማሉ ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አርሶ አደሩ ተገቢውን መረጃ አግኝቶ ምርቱን ወደ ገበያ እንዲያወጣና ለድካሙ ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ መንግስት በዘመናዊ መሳሪያ በመታገዝ ወቅታዊ መረጃ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል ። በየቦታው የመረጃ ማዕከላት በማቋቋም፣ በነፃ የስልክ መረጃ አገለግሎት ፣ በሞባይልና በአጫጭር የፅሁፍ መልእክቶች ጭምር ለአርሶ አደሩ መረጃ ለማቀበል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ። የሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃም ታደሰ እንደገለፁት ድርጅታቸው ችግሩን በማቃለሉ ሂደት የበኩሉን አስተዋኦ ለማበርከት አምራቾች ፣ ሸማቾች ፣ አቀነባባሪዎች ፣ ላኪዎች ፣ የህብረት ስራ ማህበራትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት የሁለት ቀናት  የምክክር  መድረክ በአዳማ ከተማ አዘጋጅቷል ። በመድረኩ ላይ በፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ከፍተኛ ባለሙያዎች  በግብርና ምርት ግብአት መረጃ፣ የግብይት ሂደትና የገበያ ትስስር ላይ ትኩረት ያደረገ  ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራቹና ሸማቹ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችሉ ስምምነቶች ይፈረማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም