በትራንስፖርት ዘርፍ የገቢና የወጪ ንግድን የሚያሳልጥ ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ሚኒስትሯ አመለከቱ

76
ሀዋሳ ህዳር 6/2011 የትራንስፖርት ዘርፍ መሠረተ ልማትን በማስፋፋትና ጥራቱን በመጠበቅ የገቢና የወጪ ንግድ ለማሳለጥ ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ አመለከቱ። ዘርፉ የፌዴራል፣ የክልሎችና የሁለት ከተማ አስተዳደሮችን የ2011 የመጀመሪያ ሩብ ዓመትና በሚኒስቴሩ የ100 ቀናት እቅድ ዙሪያ ዛሬ በሃዋሳ መምከር ጀምሯል።፡ ሚኒስትሯ ወይዘረሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ዘርፉ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ውጤታማ ለማድረግ ባለው ሚና ምርቶቹን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ ወሳኝነት አለው፡፡ አገራዊው ኃላፊነት ለመወጣት ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ ተቋማት ተቀናጅተው ኅብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ መንግሥት በዘርፉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ መድቦ በመንቀሳቀሱ ለውጥ ተመዝግቧል ያሉት ሚኒስትሯ፣ በመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ የባቡር ኔትወርክ፣ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዕድገትንና የኤርፖርት ማስፋፊያ ሥራዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በማሳደግ ረገድ የተመዘገበው  እመርታ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱንም አስታውቀዋል፡፡ ከአገልግሎት አሰጣጥና መሠረተ ልማት ግንባታ ጋር በተያያዘ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ብልሹ አሠራሮች መኖራቸውንም የገለጹት ወይዘሮ ዳግማዊት፣ ችግሩን ለመፍታት ባለፉት ዓመታት የተደረገው ጥረት በቁርጠኝነት ባለመፈፀሙ ተጠያቂነትን ማስፈንና ሌብነትን ከምንጩ ማድረቅ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ የትራንስፖርት አቅርቦት ከፍላጎት ጋር አለመጣጣም፣ የሥነ ምግባርና የብቃት ችግር፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጥራት መጓደል፣ የተሽከርካሪ ብቃት አረጋጋጭ ተቋማት የሥነ ምግባር ውስንነት፣ የትራፊክ አደጋ መጨመርና የሎጀስቲክ ቅንጅት ደካማ መሆን ችግሮች እንደሚታዩ ገልጸዋል፡፡ ችግሮቹን በዘላቂነት በመፍታት የኅብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ ጥረቱ ሊጠናከር እንደሚገባም ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በ100 ቀናት ሊያከናውናቸው ያቀዳቸው ተግባራት ከሕግ አንጻር የአገልግሎት አሰጣጥንማሻሻል፣ የትራንስፖርት መሠረተ ልማትን በተያዘለት ጊዜና በጥራት የሚያስፈጽሙፕሮጀክቶችን ማከናወን፣ የፖሊሲና የሕግ ጉዳዮችን የተመለከተ የትራንስፖርት ማስተር ፕላን ቢጋር ማዘጋጀት አንዱ ነው። የትራንስፖርት ፖሊሲ የማስፈጸሚያ ስትራቴጂና የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና ማጽደቅ፣ የሲቪል አቪዬሽን ፖሊሲና ዓዋጅ ጥናት በመከለስ ማጽደቅና የሎጂስቲክ ሥርዓት ሰንሰለቱን ማሻሻል በዕቅዱ የተያዘ ጉዳይ ነው። የዘርፉን የሰው ኃይል በዘላቂነት ለመገንባት ከማሰልጠኛ ማዕከላትና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የሚሰራባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን ማጠናቀቅም ትኩረት እንደተሰጠው  ተመልክቷል። የመድረኩ ተሳታፊዎች ዕቅዱን ለማሳካት በሚከናወኑ ዝርዝር ተግባራት ላይ ይወያያሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም