ሙስናና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ለማቅረብ በሚያደርገው ጥረት ሚናችንን እንወጣለን-የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች

68
ፍቼ ህዳር 6/2011 ሙስናና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን  ለህግ ለማቅረብ በሚያደርገው  ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች  ገለጹ፡፡ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎቹ እንደገለጹት መንግስት ሙስናና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን  ለሕግ ለማቅረብ እያደረገ ያለው ጥረት መጪውን ጊዜ በተስፋ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡ የአገር ሽማግሌውኮሎኔል  ገዝሙ ገቢሳ  የአገርንና የህዝብን ሀብት የመዘበሩ ብቻ ሳይሆኑ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በዜጋቸው ላይ የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን  ለሕግ ለማቅረብ የተጀመረው ጥረት እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። በቅኝ ግዛት  የተያዘ ሀገር  ላይ እንኳ  የማይፈፀም  ዘግናኝ  ዘረፋ  የመንግሥትን ሥልጣን መከታ በማድረግ ወንጀል  የፈጸሙ  ተጠርጣሪዎችን በህግ እንዲዳኙ  መደረጉ የመንግስትን አርቆ አስታዋይነት ስለሚያመለክት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አመልክተዋል ። ሕዝቡ ካለበት ድህነት ለመውጣት ሰላሙን  ከመጠበቅ ባሻገር ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ  መሰራት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡፡ የፍቼ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ  የሥነ-ልቡና ትምህርት መምህር  ጥላሁን በዳዳ  በበኩላቸው “ ታሪክ እንደሚያስረዳው  ጠንካራ ማህበረሰብ ና ትውልድ  የሚፈጠረው ቀደም ብሎ በተዘረጋው አመራር በመሆኑ  አሁን በአገሪቱ የሚከናወኑ የለውጥና የፍትህ ሥራዎች ትወልድን  በመቅረጽ  ፍሬያማ  ይሆናሉ ” የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ወጣቱ  ራሱን ከስሜታዊነትና ከጀምላ  ፍረጃ በማራቅ ለሌሎች ከበሬታና ፍቅርን በማሳየት በጸረ ሙስና ትግሉ ምሳሌ ሊሆን እንደሚገባውም   አሳስበዋል ። ወንጀለኛንና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን ለመታገል በመንግሥት  የተጀመረውን  እንቅስቃሴ ተገቢ በመሆኑ ልንደግፈው ይገባናል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። "መንግሥት  ወንጀልና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን ፈጽመዋል ያላቸውን ተጠርጣሪዎች ተከታትሎ ለፍርድ የማቅረብ  ሂደቱ አስደስቶኛል" ያለችው የፍቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ተማሪ ጥሩ ወርቅ አስፋው ናት፡፡ መርከብና አውሮፕላን  ለአገር ልማትና ጥቅም ከማዋል ይልቅ፤ ለግለሰቦች ጥቅም መዋላቸው እንዳሳዘናት ተናግራለች። ለወደፊቱም ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት የዝምድናና ወገናዊ አሰራር የሚቀርበት ዘዴ መቀየስ እንዳለበት ጠቁማለች፡፡ የሕዝብ ሀብት ያለ አግባብ ያባከኑ ተጠርጣሪዎች  በሕግ አግባብ መቀጣት አለባቸው ያለው ደግሞ  የዞኑ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር  ወጣት አበራ ጋዲሳ ነው፡፡ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ የሚያጋጥሙ  የሐሰት ወሬዎችን ከመመከት ጎን ለጎን ለውጡን ለህዝብ ተደራሽ  ለማድረግ አንደሚሰራም አስታውቋል። ወጣቱ በብረተሰቡ ውስጥ  ያለው ድርሻ  ከፍተኛ መሆኑን የተናገረው ወጣቱ፣ ፍትህን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሚናውን እንደሚወጣም አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም