የሚዛን አማን አካባቢ ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ የሃገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

129
ሚዛን ግንቦት 15/2010 በቤንች ማጂ ዞን የሚዛን አማን ከተማና አካባቢው ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ድጋፍ በመስጠት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡ በከተማውና በአካባቢው በሚገኘው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ትናንት ተከስቶ  በነበረው የጸጥታ ችግር ዙሪያ ከኃይማኖት አባቶች፣ ከሃገር ሽማግሌዎችና ከሌሎችም  ህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ዛሬ ውይይት ተካሄዷል፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወንድሙ ገብሬ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት የኃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች በአካባቢው  ሰላምን ለማረጋገጥ የሚኖራቸው ሚና የጎላ ነው፡፡ በተለያዩ የእምነት ተቋማትና ማህበረሰብ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ህብረተሰቡን ስለ ሰላም ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ከዚህ ቀደም የጸጥታ ችግር አጋጥሞ እንደሚውቅ ያመለከቱት አስተዳዳሪው ትናንት በተፈጠረው ረብሻ የንብረት ጉዳት  የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ የመለየት ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ "በቀጣይም ጥፋት ያደረሱ አካላትና የችግሩ ምክንያቶች ተለይተው ተጠያቂ የማድረግ ስራ ይከናወናል "ብለዋል፡፡ በጥፋቱ የተሳተፉትን አጋልጦ ለህግ አሳልፎ በመስጠት ህብረተሰቡ ተባባሪ እንዲሆንና የአካባቢ ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ በተለይ   የሃገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም   የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ከትናንት ጀምሮ የተቋረጡ መደበኛ የህዝብ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል የሃገር ሽማግሌው አቶ ኩንዲሳ ፓርኪ በሰጡት አስተያየት "ሁሉም የአካባቢው ነዋሪ ሰላሙ ወደነበረበት እንዲመለስ ዘብ መቆም አለበት "ብለዋል፡፡ የከተማዋን ሰላም ማደፍረስ ላይ የተሳተፉ ጥፋተኞችን አሳልፎ ለመስጠት መዘጋጀታቸውንና ህዝቡም በዚህ እንዲሳተፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡ የዞኑ ኃይማኖቶች ምክር ቤት ጸሐፊ ቄስ ሳሙኤል ወንድሙ  የአካባቢውን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደረግ ጥሪ  አቅርበዋል፡፡ በሚዛን አማንና በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ተከስቶ የነበረውን ረብሻ መቆጣጠርና አካባቢውንም ማረጋጋት መቻሉን የካፋና ቤንች ማጂ ዞኖች ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኮሎኔል ፀጋዬ አብርሃ መግለጻቸውን ቀደም ሲል መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም