የሶዶ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ የሲዳማ ተወላጅ ተማሪዎች ወላይታ ሶዶ ሲገቡ አቀባበል ተደረገላቸው

494

ሶዶ ህዳር 6/2011 በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጭ መሰረተ ቢስ ወሬ ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል ያልቻሉ ከ200 በላይ የሶዶ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ተማሪ የሆኑ የሲዳማ ተወላጆች ወላይታ ሶዶ ከተማ ሲገቡ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡

ሶዶ ከተማ ከገቡት መካከል 161 ነባር ተማሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ አዲስ የተመደቡ ናቸው፡፡

ተማሪዎቹ ዛሬ ወላይታ ሶዶ ሲገቡ የሃገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶችና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

በኮሌጁ የ3ኛ ዓመት የእጽዋት ሳይንስ ተማሪ አየሌ መቻል ለኢዜአ እንደገለጸው ባለፈው ዓመት ሰኔ 8 የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከፍተኛ የስነ ልቦና ጉዳት በማድረሱ ወደ ኮሌጁ ለመምጣት ፈርቶ እንደነበር ገልጿል፡፡

በዚህ ዓመትም ”የሲዳማ ብሄረሰብን ያነጣጠረ ጥቃት ይፈጸማል” በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው መረጃ ስጋት ፈጥሮበት ከትምህርቱ መሰተጓጎሉን ተናግሯል፡፡

ባለፈው ሳምንት ለዩኒቨረሲቲ ተማሪዎች የተደረገው አቀባበል ሀሳቡን እንዲቀይር ረድቶት ዛሬ ለመምጣት መወሰኑንና አምና በተፈጠረው ግጭትም የወላይታ ተወላጆች አልብሰውና የትራንስፖርት ገንዘብ ሰጥተው እንደሸኙት አስታውሷል፡፡

የ3ኛ ዓመት የእንስሳት ሳይንስ ተማሪዋ ገነት ደበላ በበኩሏ የገጠማት ችግር ባይኖርም  ትምህርት ከጀመረች በኋላ በማህበራዊ የትስስር ገጾች የሚሰራጩ መረጃዎች ስለረበሻት ወደ አካባቢዋ መመለሷን ገልጻለች፡፡

”ሰላማችንን መጠበቅ አለብን የምንሰማው ውሸት ነው ዛሬ የወላይታ ህዝብ ያደረገልን አቀባበል ሁሉንም የሚያስረሳና ቤተሰብ መሆናችንን የሚያመላክት ነው” ብላለች፡፡

የወላይታ ዞን ሽማግሌዎች ተወካይ ፓስተር ዮሃንስ ባሳና የወላይታና የሲዳማ ብሄረሰቦችን ለመለያየት የሚሰሩና የሚጥሩ ሃይሎች ታሪክን የማያውቁና ዘመኑ የደረሰበትን ያልተገነዘቡ ናቸው ብለዋል፡፡

”የችግሩን ምንጮች ለይተናል ተጋግዘንና ተደጋግፈን ለመኖር ወጣቶች በሰከነ መንፈስ ነገሮችን ማየትና አባቶችን መስማት ይገባችኃል” ሲሉ መክረዋል፡፡

የሲዳማ ሃገር ሽማግሌዎች ተወካይ አቶ አማረ አላንቦ ዕድሜያቸው ከ90 ዓመት ማለፉን ተናግረው በዚህ በኖሩባቸው ዓመታት እንደዚህ ዓይነት አንድነትን የሚፈታተን ችግር እንዳልገጠማቸው ገልጸዋል፡፡

”ለፖለቲካ ትርፍ የሚሯሯጡ ግለሰቦች ማንንም አይወክሉም ለማንም አይተርፉም’ ያሉት አቶ አማረ ‘ተያይዘን እንኖራለን ሰላማችንን መጠበቅ አለብን” ብለዋል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚጽፉ ግለሰቦችም ሃገር በማፍረስና ህዝብ በማጣላት የሚያገኙት ነገር ስለለሌ ቆም ብሎ ማሰብ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

”ወጣቶቻችንም ምንም በሌለበት የሚወጡ መሰረተ ቢስ ወሬዎችን ማጣራት ይገባችኃል የቀሩትም መምጣት አለባቸው” ሲሉ መክረዋል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ተወካይ አቶ አዘዘ አሊዬ መንግስት እያንዳንዱን ነገር በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

”በተለይም ሁለቱ ብሄረሰቦች ላይ በማነጣጠር ማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም የህዝቡን ስነ ልቦና የሚረብሹ ግለሰቦች አደብ መግዛት አለባቸዉ” ብለዋል፡፡

የወላይታ ህዝብና የኮሌጁ ማህበረሰብ እያደረገ ያለው አቀባበልና ተማሪዎችን ለመመለስ የተደረገው ጥረት በሁለቱ መካከል ለሰላም ያለውን ቁርኝት አመላካች በመሆኑ ተማሪዎች ትምህርታቸዉን በተረጋጋ መንፈስ እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡

በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ሽማግሌዎች ከሁለቱ ዞን ተወካዮች ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን ለሲዳማ ብሄረሰብ ተወካይ ሽማግሌዎች ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡