የትምህርት ተደራሽነት እድገቱ በጥራትም ላይ እንዲደገም የድርሻችንን እንወጣለን-- ምሁራን

116
ዲላ ግንቦት 15/2010 መንግስት ባለፉት ዓመታት በትምህርት ተደራሽነት ላይ ያስመዘገበው እድገት ጥራትም ላይ እንዲደገም የድርሻቸውን እንደሚወጡ በዲላ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን የሰጡ  ምሁራን ገለጹ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ዶክተር ሐብቴ ዱላ ለኢዜአ እንዳሉት ባለፉት 27 ዓመታት በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ በተለይ በትምህርት ተደራሽነት ላይ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው እድገት አመርቂ ነው፡፡ ለዚህም በአዲስ አበባና ጥቂት ክልሎች ተወስነው የነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ላይ ከ40 በላይ ማድረስ መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም መንግስት ባለፉት ዓመታት በትምህርት ተደራሽነት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጥራቱን ለማስጠበቅ የተሰራው ስራ አጥጋቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ብቁ መምህራንን የማፍራቱ ተግባር በቂ ትኩረት አለማግኝቱ ፤ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከህንፃ ግንባታ ባሻገር የቤተሙከራዎች አለማሟላትና ተግባር ተኮር የትምህርት አሰጣጥ ላይ ትኩረት አለማድረጋቸው ለጥራቱ መጓደል በምክንያትነት አንስተዋል፡፡ በትምህርት  ተደራሽነት ላይ የታየው እመርታ በጥራቱም እንዲደገም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸውና እሳቸውም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር አለበል ጓንጉል በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ በመስፋፋት ተደራሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ረገድ አንድ ተማሪ ከሶስት ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ሳይጓዝ መማር የሚችልበት አጋጣሚ እንደተፈጠረ በመጥቀስ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥርም መስፋፋቱን  ጠቅሰው የጥራቱ ሁኔታ በዚህ ልክ ትኩረት እያገኘ አለመሆኑን አመልክተዋል ፡፡ የተማሪዎች አመለካከት ግንባታ ላይ አለመሰራቱን ለጥራቱ መጓደል በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡ መምህር አለበል የትምህርት ፖሊሲውና ስርዓተ ትምህርቱ መፈተሸ እንደሚገባቸው አመልክተው "ምሁራን በጥራት ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ለፖሊሲ አውጪዎች አቅጣጫ ማሳየት ይገባቸዋል " ብለዋል፡፡ በዚሁ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አበራ ወንዶሰን በሰጡት አስተያየት በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ሽፋን እድገት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መምህር አበራ እንዳሉት የትምህርት ተቋማት ወቅቱን የጠበቀ ቴክኖሎጂና የትምህርት አሰጣጥ ባለመከተለቸው ጥራት ያለው ብቁ የሰው ኃይል እያፈሩ አይደለም ፡፡ የኩረጃ ባህልም የትምህርት ጥራቱን ከሚያሳንሱ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ "መልካም ስብዕና ያለውና ብቁ ዜጋ ለማፍራት ጥሩ ሥነ-ምግባር በመላበስና ወቅቱ በሚፈልገው ልክ ራሳችንን በማብቃት የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል "ብለዋል፡፡ መንግስት የትምህርት ተደራሽነት  ላይ ያስመዘገበው   እድገት በጥራትም ላይ እንዲደገም የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም