በመስቃን ወረዳ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል - የጉራጌ ዞን ፖሊስ

65
ሀዋሳ ህዳር 6/2011 በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ የተከሰተውን ግጭት ለማረጋጋት በተደረገው እንቅስቃሴ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን የዞኑ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ውደማጣስ አወል ለኢዜአ እንደገለጹት ትናንት በመስቃን ወረዳ ኢንሴኖ ከተማ በተከሰተ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን ገልጸዋል፡፡ ግጭቱ ባስከተለው አደጋ የሟቾች ቁጥር 17 መድረሱን የተናገሩት ፖሊስ አዛዡ በከባድና ቀላል ጉዳት ሆሲፒታል የገቡ ተጎጂዎች ቁጥር መጨምሩንም ተናግረዋል፡፡ በአደጋው በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ አዛዡ እንደተናገሩት የፀጥታ ሃይሉ አካባቢውን ለማረጋጋት ባደረገው እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ገልጸዋል፡፡ ዛሬ ወደመረጋጋት በመጣችው ኢንሴኖ ከተማና  አካባቢዋ የሃገር ሽማግሌዎች ችግሩን ለመፍታት ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ የፀጥታ ሃይሉ በችግሩ ምክንያት ከአካባቢያቸው እየተፈናቀሉ ያሉ ዜጎችን የማረጋጋትና የመመለስ ስራ እያነከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ''ከዚሁ ጎን ለጎንም ጥቃቱን እየፈጸሙ ያሉ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እየተከናወነ ነው'' ብለዋል፡፡ በወረዳው ትናንት የተከሰተው ግጭትና ያጋጠመውን ጉዳት እንዲሁም እየተደረገ ያለውን የማረጋጋት ሰራ ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም