ስምምነቱ በኦሮሚያ ክልል የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አስተዋጽኦ አለው- የጎባ ከተማ ነዋሪዎች

93
ጎባ ህዳር 6/2011 የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በኦሮሚያ ክልል የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የደረሱት ስምምነት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የባሌ ሮቤ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የከተማው አንዳንድ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ድርጅቶቹ ትናንት ያደረጉት ስምምነት በክልሉ ሰላምን ለማረጋገጥ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴውን ለማሳደግ ያስችላል ብለው ያምናሉ። ኦነግ ከኦሮሚያና ከፌዴራል መንግሥታት ጋር ተባብሮ ለመስራት በተለይ በክልሉ ሰላም  እንዲሰፍን ሚና እንደሚጫወት የገለጹት አስተያየት ሰጪዎች፣ለስምምነቱ ተግባራዊነት ሁሉም አካላት መተባበር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹ አቶ አብደላ ማህሙድ ድርጅቶቹ የደረሱበት ስምምነት ላይ በክልሉ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረት እንደሚያስችል አመልክተዋል። ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለመወጣት እንደሚሰሩም አመልክተዋል፡፡ ስምምነቱ በተለይ በዞኑ የተወሰኑ ወረዳዎች የጦር መሣሪያዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላማዊ ሂደት ለመለለስ እንደሚያስችላቸው የተናገሩት ደግሞ የአገር ሽማግሌው ሼህ ቃሲም ኡስማን ናቸው፡፡ ''የክልሉ ብሎም የአገሪቱ ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው የሚጠበቅብንን ግንባር ቀደም ሚናችንን እንወጣለን'' ሲሉም ለስምምነቱ ተግባራዊነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡ ድርጅቶቹ በአገርና ህዝብ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ የነበሩ ወገኖችን ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከስምምነት መድረሳቸው የልማት ፕሮጀክቶች ከግብ እንዲደርሱ አስተዋጽኦ ያደርጋል ያለው ደግሞ ወጣት አህመድ ሙክታር ነው፡፡ ወጣቱ ኃይል ከስሜታዊነት በመውጣት የለውጥ ሂደቱን በመደማመጥና በመደጋገፍ ከዳር እንዲያደርስ ጠይቋል፡፡ በኦዴፓ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ለማ መገርሳና በኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የተመራው ልዑካን ቡድኖች ትናንት በክልሉ ጸጥታ ጉዳዮችና በኦነግ ታጣቂ ስም በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ በሚፈጠሩ ግጭቶች ዙሪያ መክረው ችግሩን በጋራ የሚፈቱበት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም