ኤጀንሲው በአዲስ አበባ ጥራት ያለው ትምህርት የሚሰጡ ትምህርት ቤቶች 21 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ገለጸ

119
አዲስ አበባ ህዳር 6/2011 በአዲስ አበባ ከተማ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ኢንፔክሽን ከተደረገባቸው ውስጥ ደረጃውን የተጠበቀ ትምህርት የሚሰጡት 21 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የአስተዳደሩ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ አስታወቀ። በጥራት ችግር የተነሳ 52 ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተደርጓል። የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲና የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፤ በከተማዋ በ2010 ዓ.ም ማጠቃለያ 1ሺህ407 ትምህርት ቤቶች ላይ ምርመራ ተደርጓል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ብሩክነሽ አርጋው እንዳመለከቱት፤ ምርመራ ከተደረገባቸው 1ሺህ407 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ጥራት ያለው ትምህርት የሚያስተምሩት 299 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው። 1ሺህ106 ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታችና ጥራቱን ያልጠበቅ ትምህርት የሚሰጡ ሲሆን ይህም በመቶኛ ሲታይ 78 ነጥብ 6 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል። በሚሰጡት አጠቃላይ አገልግሎት፣ ብቁ የሰው ኃይል፣ የተሟላ ቁሳቁስ፣ ቤተ ሙከራ፣ የቤተ መጽሐፍት፣ የመጫወቻ ሜዳ፣ በቂ መጽሃፍት፣ የውሃ፣ የመጸዳጃ ቤትና ሌሎች መስፈርቶች የምርመራ ሂደቱ መስፈርቶች እንደነበሩ ገልጸዋል። በዚህም መሰረት 26 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች፣ 22 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 4 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች በመሆናቸው መዘጋታቸውን ጠቁመዋል። ለሌሎች ትምህርት ቤቶች ሞዴል የሆኑ እና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ሁለት ተቋማት ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል። የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው ሁለት የተለያየ ጥናት በከተማዋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ያለውን ችግር ለመዳሰስ መሞከሩን የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤላዘር ታደሰ ገልጸዋል። ተማሪዎች በ8ኛ ክፍል መልቀቅያ ላይ አነስተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡት ለትምህርት ባላቸው አመለካከት መሆኑን በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ 8ኛ ክፍል ፈተና ዝቅተኛ እንዲሆን ካደረጉት መካከል፣ ተማሪዎቹ ለትምህርት ያላቸው ዝቅተኛ አመለካከት መሆኑን ገልጸዋል። ''በአዲስ አበባ ከተማ በ7 እኛ 8 ክፍል ተማሪዎች ላይ በተደረገ ጥናት ተማሪዎች ከትምህርት ይልቅ ለገንዘብ ትኩረት እንደሚሰጡና ቢማሩም ባይማሩም ገንዘብ ማግኘት እንደሚችሉ ያምናሉ'' ብለዋል ምክትል ፕሬዚዳንቷ። በከተማ አስተዳደሩ የ8ኛ ክፍል ዝቅተኛ የሆነባቸው ምክንያት በተማሪዎች፣ በመምህራንና በተማሪ ቤተሰቦች ላይ በተሰራ ጥናት ተማሪዎች ለትምህርት ዝቅተኛ አመለካከት እንዳለቸው ለማወቅ ተችሏል። ''በዚህም ውጤቱ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል ተማሪዎች ትምህርት ባንማር ገንዘብ ማግኘት እንችላል የሚል አመለካከት መያዛቸው ነው'' ብለዋል። ሌላው ችግር ደግሞ የሚያስተምሩ መምህራን ብቃት አጠያያቂ መሆን፣ የቤተሰቦች ለተማሪዎች ክትትል አለማድርግ፣ የትምህርት ቤቶች አስተዳደር ተማሪዎችን ለመከታተል እና ድጋፍ ያለማድርግና፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽህኖ ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አድርጓል። ሁለተኛው ጥናት ላይ ዩኒቨርሲቲው በአጠቃላይ የሚሰጠው ስርዓተ ትምህርቱ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች ጋር  በአብዛኛው ተመሳሳይ ቢሆንም በአካባቢ ሳይንስ ላይ የተወሰኑ ልዩነት ስላለው ለወደፊት ከከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በመመካከር መፍታት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም