በመዲናዋ ከ300 በላይ ህንፃዎች ከውል ውጭ የግንባታ ማስፋፊያ አድርገዋል

115
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010  በአዲስ አበባ ከ300 በላይ ህንፃዎች ከውል ውጭ የግንባታ ማስፋፊያ አድርገው መገኘታቸውን የአዲስ አበባ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። ህንፃዎቹ ከከተማዋ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የማሻሻያ ፈቃድ ሳያገኙ ማስፋፊያና ወለል ጨምረው የተገኙ መሆናቸው ተገልጿል። ባለስልጣኑ በሰራው የዳሰሳ ጥናት ከውል ውጭ ግንባታ አድርጎ መገኘት ለህንፃ ግንባታ ጥራት ማነስ ዋነኛው ችግር መሆኑን የባለሰልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መለሰ አለቃ ገልፀዋል። ፈቃድ ሳያገኝ ወለል መጨመርና ግንባታ ማካሄድ በአዋጅ የተከለከለ ቢሆንም በከተማዋ የማስፋፋትና ወለል የመጨመር ችግሮች መስተዋላቸውን አስታውቀዋል። ፈቃድ ሳያገኙ የተገነቡ ህንፃዎች በሙሉ እንዲመዘገቡ በወጣው የሶስት ወር ማስታወቂያ ከ300 በላይ ህንፃዎች መመዝገባቸውን ነው የገለፁት። የተመዘገቡት ህንፃዎች አማካሪዎች፣ ኮንትራክተሮቹና ባለቤቶቹ ህንፃው ጉዳት ቢያደርስ ኃላፊነቱን ለመውሰድ የውዴታ ግዴታ ይገባሉ ብለዋል። በማስታወቂያ ጥሪው ያልተመዘገበና ከዚህ በኋላ ከፈቃድ ውጭ ገንብቶ ከተገኘ አማካሪው፣ ተቋራጩ እና ባለቤቱ በአዋጁ መሰረት ለህግ ይቀርባሉ ብለዋል። በሌላ በኩል የዴሊቨሮሎጂ አሰራር ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ በግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር አገልግሎት በኩል ከፍተኛ መሻሻል እንደተገኘ ገልፀዋል። በከተማዋ ከፍተኛ ችግር አለባቸው ተብለው በደሊቨሪ ዩኒት ከተያዙ መስኮች አንዱ የግንባታ ቁጥጥርና ፈቃድ አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰው የፕላን ስምምነት፣ የህግ ማዕቀፍ፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ላይ ያሉ ብልሹ አሰራሮችን ጨምሮ 10 ችግሮች ተለይተው በደሊቨሪ ዩኒት ተሰርቶባቸዋል ብለዋል። ችግሮቹን ለመቅረፍ የተወሰዱት እርምጃዎችም የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጠት እና የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት መስጠት መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም በቀድሞው አሰራር የፕላን ስምምነት ለመውሰድ ከአንድ ሳምንት እስከ ሶሰት ወር ይወስድ እንደነበር ገልፀው አሁን ላይ በአንድ ማዕከል አገልግሎቱን ለማግኘት የሚፈጀው ጊዜ ከ45 ደቂቃ እንደማይበልጥ ተናግረዋል። ደንበኞች የግንባታ ፈቃድ ለመውሰድ ቢሮ መመላለስ ሳይጠበቅባቸው ኢንተርኔትን በመጠቀም በኦንላይን መመዝገባቸው እስከ ሶስት ወር ይፈጅ የነበረውን ጊዜ ወደ አንድ ሳምንት አሳጥሮታል ብለዋል። ባለስልጣኑ በዚህ ዓመት 500 አዳዲስ የግንባታ ፈቃድ መስጠቱንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም